የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮርያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጥል አሜሪካና ጃፓን ጠየቁ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ለስድስተኛ ጊዜ የሃይድሮጅን ጦር መሳሪያ ሙከራ ባካሄደችው ሰሜን ኮርያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጥል አሜሪካ እና ጃፓን ጠየቁ ፡፡

ሩሲያ በበኩሏ በሰሜን ኮርያ ላይ አዲስ ተጨማሪ ማዕቀቦችን መጣል ለውጥ አያመጣም ብላለች።

ፒዮንግያንግ ጃፓንን ያቋረጠ ሚሳኤል ማስወንጨፏንና በተለይም በከርሰ ምድር የሀይድሮጅን ቦምብ ሙከራ አካሄደች ከተባለ በኋላ የኮርያ ልሳነ ምድር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ፖለቲካዊ ውጥረቱ እያየለ መጥቷል፡፡

በዚህ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አሜሪካና ጃፓን በሃገሪቱ ላይ አዲስና ጠንካራ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ጠይቀዋል፡፡

በኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር የዓለምን ጊዜ ሊያጠፋ እንደማይገባም አስታውቀዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እኤአ ከ2006 ዓም ወዲህ የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮርያ ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች እንዳልሰሩ እና የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጦርነት እንዲከፈት በመተንኮስ ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።

አምባሳደሯ ኒኪ ሄይሊ አሜሪካ በምታቀርበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ በዝርዝር ባይገልጹም ፒዮንግያንግ ከማንኛውም ሀገር የነዳጅ አቅርቦት እንዳታገኝ ማድረግ በማዕቀቡ ሊካተት እንደሚችል ከዋይትሃውስ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

የሀገሪቱን ብሔራዊ አየር መንገድ ማገድ፣ በውጭ ሀገራት የሚሰሩ ሰሜን ኮሪያውያንን ከስራ መቀነስ፣ የባለስልጣናቷን ሀብት ማገድና ጉዞ መከልከል በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል።

ምንም እንኳ ማዕቀቡ በፍጥነት እንዲጣል አሜሪካ ጀርመን ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ቢጠይቁም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን በሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ተጨማሪ ማዕቀቦችን መጣል ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ባካተተው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል ፒዮንግያንግን ከኒዩክሌር ፕሮግራሟ እንድታቆም አያደርጋትም ብለዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን ሰሜን ኮርያ ያደረገችውን የኒዩክሌር ቦምብ ሙከራ ግን  አውግዘዋል፡፡

ይሁን እንጅ ዜጎችን የሚጎዳ ማዕቀብ ከመጣል ይልቅ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው ወገኖች በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው መፍታት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ቻይና በበኩሏ በኮርያ ልሳነ ምድር የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊና በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ ማስቀመጡ ብቸኛው አማራጭ ሊሆን ይገባል የሚል አቋም አላት።

እ.ኤ.አ ከ19 50 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ከተካሄደው የሁለቱ ኮርያዎች ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ጎረቤታሞቹ በባላንጣነት ሲተያዩ ለዘመናት ዘልቀዋል። 

እናም ይህ ለዘመናት የዘለቀው የኮርያ ልሳነ ምድር ቆርሾ  ዓለምን  በድጋሚ ወደ ጦርነት ያስገባት  ይሆን የሚለው ስጋት የበርካታ ዓለም ሃገራትን አስጨንቋል፡፡ 

ሰሜን ኮሪያ ለ6ኛ ጊዜ ባካሄደችው የሚሳኤል ሙከራ የተሳካ የሃይድሮጅን ቦምብ ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ ሃገሪቱ ለጦርነት እየተዘጋጀች ነው የሚል ስጋትን የፈጠረ ሲሆን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን የኮሪያ ልሳነ ምድር አንዱ ሌላዉን ከማስፈራራት አልፎ ዳግም ዋጋ ወደሚያስከፍል ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደማይገቡ ያነሳሉ፡፡ ( ምንጭ:ቢቢሲ)