ሰሜን ኮርያ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጃፓን የባላስቲክ ሚሳኤል አወናጨፈች

ሰሜን ኮርያ ላይ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት ሰሞኑን የነዳጅ ምርትን እንዳታስገባ ፤ጨርቃ ጨርቅን ወደ ውጭ እንዳትልክ እንዲሁም ዜጎቿ ወደ ተለያዩ አገራ ሄደው እንዳይሰሩ የሚከለክል ማዕቀብ መጣሉ ይታወቃል፡፡

ማዕቀቡን ተከትሎ ሰሜን ኮርያ ቅሬታዋን ያሰማች ሲሆን አሜሪካን ትልቅ ዋጋ የሚስከፍል እርምጃ እንደምትወስድም ዝታ ነበር፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብ ቢያጠነክረን እንጂ አያዳክመንም ሲሉም መሪዋ ኪም ዮንግ ኡን መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

ጃፓንን በማጥፋ አሜሪካንን ወደ አመድ በመቀየር ታሪክ እንሰራለን በማለትም ዝተዋል፡፡ ምንም ዓይነት ኃይል ከእርምጃቸው ሊያቆማቸው እንደማይችል በተደጋጋሚ ሲናገሩም ተሰምቷል፡፡

አሁንም ታዲያ ፒዮንግያንግ የተናገረችውን ከመተግበር ወደ ኋላ አለማለቷን የሚሳይ እርምጃ የተባለውን ድርጊት ፈፅማለች፡፡ እናም ሰሜን ኮርያ በጃፓን ላይ የባላስቲክ ሚሳኤል ማወናጨፏ ተሰምቷል፡፡ ይህም በሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ሙከራ ነው ተብሏል፡፡

የደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ክፍል ሚሳኤሉ በ770 ኪሎ ሜትር ከፍታ 3 ሺ 700 ኪሎ ሜትር ተጉዞ በሆካይዶ የጃፓን ባህር ማረፉን አስታውቋል፡፡

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አገራቸው ከአሁን በኋላ ትግስቷ መሟጠጡንና የሰሜን ኮርያን የፀብ አጫሪነት ድርጊት ዝም ብላ እንደማትመለከት ተናግረዋል፡፡

ፒዮንግያግ በያዘችው የእብሪት መንገድ የምትቀጥል ከሆነ ቀጣዩ ጉዞ በጭለማ የተወጠ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም ሲሉም ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በበኩላቸው የመንግስታቱ ድርጅት ህግን የተጣረሰው የፒዮንግያግ ድርጊት በጣም አሳዛኝና ፀብ አጫሪነቷን በገሀድ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የሰሜን ኮርያ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አጋር የሆኑት ቻይናና ሩስያ ፒዮንግያንግ እንዳሻት የምታወናጭፈውን ሚሳኤል እንድታቆም በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን ያህል አለመወጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተወናጨፈው ሚሳኤል በጃፓን መርከቦችና ጦር አውሮፕላኖች ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩን የሚመለክት መረጃ እንዳልደረሳት ጃፓን አስታውቃለች፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚቀመጥ ቢበቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡

ፒዮንግያንግ የሃይድሮጅን ቦምብን ጨምሮ የተለያዩ አህጉር ተሻጋሪና የተለያዩ ርቀት መጓዝ የሚችሉ የሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡( ምንጭ: ቢቢሲ)