ቻይናና የደቡብ ምስራቅ እስያ አገራት የንግድ ትስስር የሚፈጥሩበት ስልት ፈጠሩ

የቻይና እና የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ብሔራዊ ማህበራት በኢንተርኔት የንግድ ትስስር የሚፈጥሩበት ሲልክ ሮድ ተብሎ የሚጠራው ስልት ፈጥረዋል፡፡

 የንግድ አሰራሩ በአባል ሀገራቱ ያሉ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትን የሚያበረታታ እንደሆነ ታምኗል፡፡

በደቡብ ቻይና ሻንግሹንግ በተደረገው 14ኛው የቻይና እና የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ብሔራዊ ማህበራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባዔ ድንበር ተሸጋሪ ንግድን ለማስፋፋት አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

ለዚህ ደግሞ የሀገራቱ ብሔራዊ ማህበራት የንግድ ትስስር የሚፈጥሩበት መንገድ ማስፈለጉ አልቀረም፡፡ ኢ ኮሜርስ ሲልክ ሮድ ተብሎ የሚጠራ በመረጃ መረብ የሚታገዝ የግብይት ስርአት ፈጥረዋል፡፡

አዲሱ ስርአት ሀገራቱ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ከማገዙ በላይ የንግድ ግንኙነቶቻቸውን ለማጠንከር እንደሚረዳ ታምኗል፡፡

ይህ ደግሞ በቻይና እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ማህል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከሩም ባለፈ አዳዲስ የንግድ አጋሮችንም ለመፍጠር እንደሚረዳ ነው የተገለፀው፡፡

በዚህ አሰራር አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፕሮግራሙ ዋነኛ ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢንተርፕራይዞች ምርቶች በቻይና የሽያጭ ምርመራ ቡድን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መመዘኛ ተቋማት ክትትል  እና ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ  የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ይደረጋልም ተብሏል፡፡

አሁን የተዘጋጀው መድረክ በቻይና እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት መካከል ያለውን ነፃ የንግድ መስመርን  ዲጂታል ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

በመስከረም መጀመሪያ ላይ በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የሚገኙ ዘጠኝ የእስያ ሀገራት የጤና መጠበቂያ ምርቶች፣ የትራስ ልብሶች፣ የወተት ዱቄት፣  የተለያዩ የምግብ እና የመጠጥ ምርቶች የሚገኙባቸው 1ሺ 166 የሸቀጣ ሸቀት ዓይነቶችን የያዙ 1ነጥብ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ትዕዛዞችን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት ጋር በተያያዘ ድንበር ተሻጋሪ የድህረ ገጽ ንግድ በቻይና እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት መካከል ያለው  የንግድ እንቅስቃሴ አዲስ መልክ እየያዘ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ 

ኢንዶኔዥያ፣ ቬትናም እና ማሌዥያ ከደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በግብይት መጠን ከፍተኛውን ደርሻ ይይዛሉ፡፡ ሃገራቱ ወደ ውጭ የሚልኳቸው የግብይት መጠን በቅደም ተከተል 49ነጥብ6 ፣ 18ነጥብ 9፣ እና 13ነጥብ 3 ከመቶ ደርሷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የንግድ ልውውጥ ከ 450 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ የኤልክትሮኒክስ ንግድን ለማስፋፋት ያለው ዕድል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል ተብሎለታል፡፡

በደቡብ ምስራቅ እስያ ከ260 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚጠቀሙ ይገመታል፡፡

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ  አጋማሽ አካባቢ ቻይናውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ 750 ሚሊዮን በላይ የነበረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት በኢንተርኔት ይገበያያሉ፡፡

በኢንተርኔት ግብይቶች ከ3ነጥብ 1 ትሪሊዮን ዩአን ወይም 474 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም በዓመት ውስጥ በ33 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የዘገነው የቻይና አለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ  ሲጂቲኤን ነው፡፡