72ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ

72ኛው የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ።  

በጉባኤው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በዘንድሮው 72ኛ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የቻድ ሀይቅ ተፋሰስ አካባቢዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችም ከምታቀርባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

ተመድ በቀጣይ ቀናቶች ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት የሚመክር ሲሆን፥ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ላለችው ኢትዮጵያ ስብሰባው ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል።

የዘንድሮው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የመካከለኛው ምስራቅን፣ አፍሪካን፣ አውሮፓን እና ሌሎችንም አህጉራት እየናጠ የሚገኘው ሽብርተኝነት እንደቀደምት ጉባኤዎች ሁሉ ትኩረት እንደሚያደርግበት ነው  የሚጠበቀው።

ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤው የፓሪሱ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ቀጣይነትን ተንተርሶ ሀገራት የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የገቡትን ቃል በሚያድሱበትና ዳግም በሚያጤኑበት ሁኔታ ዙሪያም ይወያያል፡፡

የሰሜን ኮሪያ ፀብ አጫሪነትና ተደጋጋሚ የኒውክሌር ማስወንጨፍ ተግባርም ውግዘት እንደሚገጥመው ከወዲሁ ተገምቷል፡፡

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ስጋት የደቀኑ ችግሮች፣ የእድገት እንቅፋቶች፣ የጤና ስጋቶች እና የርዕዮት ዓለም ልዩነቶች ቀርበው በጉባኤው ሰፊ ውይይት ያካሂድባቸዋል።

በጉባኤው በሰላም ማስከበር ዙሪያ ምክክር የሚደረግ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የወሩ ፕሬዝዳንት እንደመሆኗ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንደሚመሩት ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ጾታዊ ጥቃትንና ትንኮሳን በተመለከተ ከ72ኛው ጉባዔ ጎን ለጎን ባዘጋጁት ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ፥ዋና ፀሃፊው ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ጾታዊ ጥቃትንና ትንኮሳን ለመከላከል የወሰዷቸውን እርምጃዎችና የአመራር ቁርጠኝነታቸውን አድንቀዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ማንኛውንም ዓይነት ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም  ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ፖሊሲ ተፈጻሚነት ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡

በልላ በኩል ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ከሚያዋጡ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደመሰለፏ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ሴቶችና ህጻናት ከጥቃት የመጠበቅ ማህበራዊ ኃላፊነትን በአግባቡ እየተወጣች እንደምትገኝም ነው የተናገሩት፡፡

ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ማክበር የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወታደሮች ለግዳጅ ከመሰማራታቸው በፊት ጾታዊ ጥቃትንና ተንኮሳን ጨምሮ በሌሎች ተያያዥ ነጥቦች ዙሪያ ተገቢ ስልጠና እንደሚያገኙ ተቅሰዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች ሲደርሱም የማጣራት ስራዎች እንሚከናወኑ አውስተው፥ እስካሁን የቀረቡ አቤቱታዎች ግን ተጨባጭነት የሌላቸው እንደሆኑ ነው ያብራሩት፡፡

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ በተካሄደው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ እንዲሁም የኬንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ተሳትፈውበታል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት ቆይታ የአገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ እንደሚያደርገው የሚጠበቅ ሲሆን፥  የአሁኑ ጉባኤም አገሪቱ ከአፍሪካ አልፋ ለዓለም ሰላም አበክራ እንድትሰራና የራሷን አጀንዳ ቀርፃ ለተቀረው ዓለም እንድታቀርብ መልካም አጋጣሚን  እንደሚፈጥርም ይጠበቃል፡፡

ለማንኛውም 193 አባል ሀገራት በመሪዎቻቸው ደረጃ የሚታደሙበት 72ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠናቀቅም  የተለያዩ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሏል፡፡