በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮች እና አማፂያን ማህል በተቀሰቀስ ግጭት ቢያንስ 19 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ ፡፡

አማፂያኑ ቀድሞ በሃገሪቱ መንግስት እጅ የነበረችውን ኒያልዱሂን የተባለን አካባቢ ተቆጣጥረናል ብለዋል፡፡

እኤአ በ2011 ከሱዳን ተነጥላ ነፃነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከተቀናጀች ከሁለት ዓመታት በኋላ ዳግም ሰላም ርቋት በታመሰ ላይ ትገኛለች፡፡

ሃገሪቷ እርቀ ሰላምን ለማውረድ የተለያዩ ድርድሮችን ብታከናውንም የዜጎቿን ሰላም ማስጠበቅ ግን አልተቻላትም፡፡ 

በተለይም የቀድሞው የሃገሪቱ ምክትል ርዕሰ ብሔር የነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር ሥልጣናቸውን ካጡ በኋላ የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ጦር የሚል ቡድን በመመስረታቸው ሃገሪቱ ወደ አስከፊ ግጭት ተመልሳ መግባቷ አይዘነጋም፡፡

በቅርቡ እንኳን ሪክ ማቻርን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ድርድር ለማከናወን ቢታቀድም አሜሪካ በሶስት ባለሥልጣናቶች ላይ በጣለችው ማዕቀብ ምክንያት ሌላ ፈተና የተደቀነባት ይመስላል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የደቡብ ሱዳን አማፅያን እና የሃገሪቱ መንግስት መከላከያ ሠራዊት ባደረጉት የአንድ ሰዓት ውጊያ ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡

የአማፂያን ቡድኑ ምክትል ቃል አቀባይ ፓውል ጋብሬል ላም ለሱዳን ትሪቡን እንዳሉት ከሆነ  ኒያልዲሂን በምትባል አካባቢ በተደረገው ውጊያ ከሁለቱም ወገኖች 19 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የአካባቢው ኮማንደር ቲቶ ቤይልን ጨምሮ በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቷል፡፡

ምክትል ቃል አቀባዩ አክለውም ከተማዋን እንደተቆጣጠሩ እና 36 ኤ ኬ 43ኤስ የተባለ የጦር መሣሪያን ጨምሮ ቀላል እና ከባባድ መሳሪያዎችን መያዛቸው ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን መንግስት በበኩሉ ውግያው መከናወኑን ጠቅሰው ኒያልዲሂን መልሰው በቁጥጥራቸው ሥር እንደሚያውል አስታውቋል፡፡

ንፁሃንን በመጠቃታቸው እና ንብረታቸው በመዝረፉ የደቡብ ሱዳን መንግስት አማፂያኑን ተጠያቂ አድርጓል፡፡                   

በተያያዘ ዜና የደቡብ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የጎግሪያል ግዛት አስተዳዳሪ ስራ እንዲለቁ አድርገዋል፡፡ በምን ምክንያት እንደሆነ ግን የሱዳን ትሪቡን ዘገባ አይገልጸም፡፡ ( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን)