ፈረንሳይ በአውሮፓ ጠንካራ የተባለ አዲስ የፀረ ሽብር ህግ አፀደቀች

ፈረንሳይ  በቀጣይ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ያራዘመችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመነሳቱ በፊት ጠንካራ የተባለውን የፀረ ሽብር ህጉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደምታደርግ አስታወቀች ።

ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ የሽብር ጥቃት ተጠርጣሪዎችን የመኖሪያቤት መበርበርን ጨምሮ ተጠርጣሪዎች የሚገኙበት ሥፍራ ድረስ በመዝለቅ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ዕድልን ይሰጣል የተባለው ይህ የፀረ ሽብር ህግ ድጋፍና ተቃውሞን በማስተናገድ ላይ ነው ፡፡

የፈረንሳይ የፀረ ሽብር ህግ እኤአ ከ1986 በኋላ ከ14 ጊዜ በላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

ይሁንና ፈረንሳይ በእነዚህ ጊዜያት ሽብርን ለመከላከል የወሰደቻቸው እርምጃዎች አንድም ልል በመሆናቸው አልያም የሀገሪቱ ውሳኔዎች አሸባሪ አካላትን  ለበቀል እርምጃዎች የገፋፉ ነበሩ ሲሉ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይናግራሉ ፡፡

በዚህም  ምክንያት ሀገሪቱ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች እንድትናጥና የምትፈልገውን ሰላም ለማግኘት እንድትቸገር  አድርጓል ይላሉ፡፡

በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የአሸባሪው አይ ኤስ ቡድን አባላት እኤአ በህዳር ወር 2015 ላይ በፓሪስ በፈፀሙት የሽብር ጥቃት የ130 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነው።

ከዚያ ጊዜ በኋላም ለበርካታ ጊዜያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲራዘም ቆይቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በፈረንሳይ ውስጥ በተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች 239 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ተከትሎም፥ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ሀገሪቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

በታሪክ የ1960ዎቹን የአልጄሪያው ጦርነት ተከትሎ ለተከታታይ ጊዜያት ከተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመቀጠል የፈረንሳዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለበርካታ ጊዜያት የተራዘመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተሰኝቷል፡፡

አሁን ታዲያ የፈረንሳይ የታችኛው ምክር ቤት ሀገሪቱ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ጥላው የቆየችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያከትም በሚል አዲስ ጠንካራ  የፀረ ሽብር ህግ ማፅደቁ ተነግሯል።

አዲሱ የፀረ ሽብር ህግ ሥልጣን የተሠጣቸው አካላት ሁሉ አስቸኳይ ጥምረት በመፍጠር በሽብር ድርጊት ላይ ተገቢውን  እርምጃ እንዲወስዱ የሚግዝ ነው ተብሏል። 

የፀረ ሽብር ህጉ ያለፍርድቤት ትዕዛዝ የሽብር ጥቃት ተጠርጣሪዎችን የመኖሪያቤት መበርበርን ጨምሮ ተጠርጣሪዎች የሚገኙበት ስፍራ ድረስ በመዝለቅ በቁጥጥር ስር ለማዋል ዕድልን ይሠጣል፡፡

በቅርቡ የተራዘመው የሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እኤአ በጥቅምት 28፣ 2017 የሚጠናቀቅ በመሆኑ አዲሱ  የፀረ ሽብር ህግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይተካል ነው የተባለው፡፡

የፈረንሳይ ፓርላማ አዲሱን የፀረ ሽብር ህግ በ415 ድጋፍ፣ በ127 ተቃውሞ እና በ19 ድምፀ ተዓቅቦ አፅድቋል፤ ይሁንና አዲሱ የፀረ ሽብር ህግ ድጋፍና ተቃውሞን በማስተናገድ ላይ መሆኑን ነው ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ የሚገኙት፡፡

በርካታ ፈረንሳውያን በፀረ ሽብር ህጉ መደሰታቸውን እየገለፁ ቢሆንም፤ ይህ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ  የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች  ህጉ ሽብርተኝነትን ለመግታት የሚፈይደው ነገር የለም፤ይልቁን ፖሊስ አላስፈላጊ ሥልጣን እንዲያገኝ ያደረገ ነው ሲሉ ህጉን አጣጥለዋል፡፡

የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ጀራርድ ኮሎምብ ሀገሪቱ አሁንም በከፍተኛ የሽብር ስጋት ውስጥ ትገኛለች በመሆኑም የፀረ ሽብር ህጉ በዚህ ደረጃ ጠንካራ ማድረግ አስፈልጓል ብሏል፡፡

 

የፀረ ሽብር ህጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት እንኳን በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ አቅራቢያ በቤት ውስጥ የተሰራ ቦምብ የተገኘባቸው አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው  ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ ባለፈው ዕሁድ በደቡባዊ ፈረንሳይ ማርሴል ከተማ አንድ ሰው ባደረሰው ጥቃት ሁለት ወጣት ሴቶች መግደላቸው ይታወሳል፡፡

ለማንኛውም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተደጋጋሚ የሽብር ሰለባ እየሆነች የመጣችው አውሮፓዊቷ ሀገር ለሽብርተኝነት ጠንካራ አፀፋ ምላሽ ይኖረዋል ያለችው  አዲሱ የፀረ ሽብር ህግ ላይ ተስፋዋን አኑራለች፡፡ ( ምንጭ: አልጀዚራነና ቢቢሲ)