በሪያድ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የተተኮሰው ሚሳኤል መክሸፉ ተገለጸ

በሳውድ አረቢያ ሪያድ ከተማ በሚገኘው የንጉስ ካሊድ አለም አቀፍ አየር ማረፊያን ለማውደም  ከየመን  የተተኮሰው  ቦለስቲክ  ሚሳኤል  በሳውድ አረቢያ  መንግሥት ጥረት መክሸፉ ተገለጸ ። 

ባለፈው ቅዳሜ በጦርነት እየታመሰች ካለችው የመን በ1200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው የሳውድ አረቢያ ርእሰ መዲና ሪያድ የሚገኘውን የንጉስ ካሊድ  አለም አቀፍ አየር ማረፊያን ለማውደም ኢላማ አድርጎ የተተኮሰው ባለስቲክ ሚሳኤል በሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጥረት መክሸፉ ተገልጻል፡፡

የሪያድ ነዋሪዎች የተተኮሰው ሚሳኤል በዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው አቅራቢያ ከፍተኛ  ፍንዳታ ያስከተለ መሆኑን ቢገልጹም ባለስልጣናት ግን አደጋው ምንም አይነት ጉዳት አለማስከተሉን ነው የተናገሩት፡፡

ሳውድ አረቢያ እንዳስታወቀችው በሀገሪቱ እና በኢራን መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ከየመን ጋር የምትጋራቸውን የየብስ፤የባህር እና የአየር ድንበሮች የዘጋች ሲሆን የሀገሪቱን ዋና ከተማ ሪያድን ኢላማ አድርጎ ለተተኮሰው ሚሳኤል በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማጺያንን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡

ባለፈው ሰኞ መቀመጫውን በየመን ያደረገው የሁቲ አማጺያን ቡድን  የሪያድ አለም አቀፍ አየር ማረፊያን ለማጥቃት ኢላማ አድርጎ የተተኮሰውን ባለስቲክ ሚሳኤል ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ኢራንን በጦር ወንጀለኛነት ከሳለች፡፡

የባላስቲክ ሚሳኤል ተኩስ በሳውድ አረቢያ ደቡባዊ ድንበር አካባቢ  እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን እና አለመረጋጋቶችን  ተከትሎ  አማፅያኑ ሪያድ  ለመድረስ ያደረጉት  የመጀመሪያ ሙከራ ነው ተብሏል፡፡ ሙከራውም የአየር ትራፊክ አደጋን እንዳስከተለ ተገልጻል፡፡ 

የሳውዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዴል አል-ጁቤር እንደገለጹት መንግስት የኢራን አገዛዝ  የፈጸመውን የሽብር ጥቃት አስመልክቶ  በጊዜው ምላሽ የመስጠት መብት አለው ብለዋል፡፡

የሳውዲ ሱኒ አመራሮች እና የኢራን ሁቲዎች በመካከለኛው ምስራቅ ከየመን እስከ ሶሪያ እንዲሁም  ከኳታር እስከ ሊባኖስ እየተስተዋሉ ባሉ አለመግባባቶች እና ጦርነቶች የተነሳ ውጥረቱ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

ባለፈው እሁድ የሳውዲ ንጉስ እና ሌሎች ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናትን የያዘች ሄሎኮፕተር በየመን ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ አሲር በተባለች ቦታ መከስከሷ የተገለፀ ሲሆን በአደጋውም የአሲር ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት የንጉስ ማንሱር ቢን ሞቅረን እና ከንጉስ ሳልማን  በፊት  የአሲር  ግዛት አስተዳዳሪ  የነበሩት ንጉስ ልጅም መሞታቸው ተዘግቧል፡፡

የአደጋው መንስኤ በውል ባይታወቅም ታዛቢዎቹ እንደገለጹት 38 የሚሆኑ የሀገሪቱ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ፣ ሚኒስትሮችን፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ነጋዴዎች በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ ከዋሉ በኋላ የተከሰተ ሲሆን ንጉስ ሞቅረንም  ከሀገሪቱ  ለመኮብለል  እየሞከሩ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቀጣናው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሚያስተሳስረውን  የጋራ አላማ ለማሳካትና ኢራን በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለመገደብ ከሳውዲ አረቢያ ጎን መሰለፋቸውም ተመልክቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሳዑዲው ንጉስ በላኩት ደብዳቤም ሳውዲ አረቢያ አክራሪነትን ለመዋጋት በምታደርገው ጥረት አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲል የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ ነው፡፡