የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ማንጋዋ በእምነት ማጉደል ከሥልጣን መነሳታቸው ተገለጸ

የዙምቧቡዌው ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ማንጋዋ እምነት አጉድለዋል ተብለው ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ተገለፀ፡፡

እርምጃው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ባለቤታቸውን ወደ ምክትል ፕሬዚደንትነት ለማምጣት የቀየሱ ስልት እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል፡፡

የዙምባብዌ ገዢው ፓርቲ ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ወደ ሥልጣን ከመጣበት እ.ኤ.አ ከ1980 ጀምሮ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ማንጋዋ የፕሬዚደንቱ የቅርብ አማካሪ እና በተለያዩ የሥልጣን መንበሮች የቀኝ እጃቸው በመሆን አገልግለዋል፡፡

የ75 ዓመቱ ምክትል ፕሬዚደንትነቱ የሥልጣን ከቀድሞው ጆይስ ሙጁሩ ከተረከቡበት ከ2014 ወዲህም የሙጋቤ ቅርብ ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ 

ሰውየው እምነትን በማጉደል እና በሙስና ቅሌት ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፓርቲው ሲታይ ከከረመ በኋላ፤ ፕሬዚደንቱ ታማኝ አገልጋያቸውን ከሥልጣን እንዲወርዱ ማድረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አንዳንዶች እንደሚሉት የማንጋዋ መጠርጠር ከበስተጀርባው ሌላ ሴራ ይኖረዋል እንጂ ግለሰቡ ከተጠረጠሩበት ድርጊት ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም ይላሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ፕሬዚደንት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ከሚንቀሳቀሰው ወገን ጋር ማንጋዋ ግንኙነት እንዳላቸው በመጠርጠራቸው ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡

ያም ሆነ ይህ ሰውየው እምነት አጉድለዋል ተብለው ከፓርቲያቸው በመጣው ውሳኔ መሠረት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡

ቢቢሲና ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት እንዳለው ከሆነ ደግሞ ሰውየው ከሥልጣን እንዲለቁ የተደረገው ቀዳማዊት እመቤትን ምክትል ፕሬዚደንት ለማድረግ ታስቦ ነው ይላሉ፡፡

የፕሬዚደንት ሙጋቤ ባለቤት የ52 ዓመቷ ግሬስ ሙጋቤ የፓርቲያቸው የሴቶች ሊግ መሪ ሲሆኑ የፖለቲካ እውቀታቸው ግን እምበዛም እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

ወይዘሮ ግሬስ ምክትል ፕሬዚደንት የመሆናቸው ወሬ እንደተሰማ በአገሪቱ ጉርምርምታን መፍጠሩ ተሰምቷል፡፡

ሙጋቤ ባለቤታቸውን ምክትላቸው ማድረጋቸውን፤ ከእድሜያቸው መግፋት ጋር የሚያያዙም አሉ ይላል ቢቢሲ፤ ዕድሜ ጠገቡ ፕሬዚዳንት ሥልጣናቸውን ለባለቤታቸው ለማስረከብ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በተጠና መንገድ ምክትላቸውን ከስልጣናቸው አንስተዋል ይላሉ የሰውየውን መነሳት የሚቃወሙ ወገኖች፡፡

ገዢው ፓርቲ በሚቀጥለው ወር በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤው የቀዳማዊት እመቤትን የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣን ሹመት ያፀድቃል መባሉን የአገሪቱን የመረጃ ሚኒስቴር ጠቅሶ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡