በየመን ግጭት 70 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ እርዳታ ጠባቂ እንዲሆን ማድረጉ ተመለከተ

እ.ኤ.አ በ2015 የተነሳው የየመን የእርስ በእርስ ግጭት ያስከተለው ቀውስ 70 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ እርዳታ  ፈላጊ እንዲሆኑ  ማድረጉ  ተገለጸ ።

በየመን ለረሃብ ድርቅ እና መታረዝ የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር መበራከት፣ የመናውያን ወደ ጎረቤት አገራት ለስደት መዳረጋቸው እንዲሁም ለበርካቶች ሞት እና የአካል ጉዳት ምክንያት የሆነው አለመረጋጋቷ ለመላው ዓለም የራስ ምታት የሆነ ይመስላል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ማርክ ላውኩክ እንዳሉት አገሪቱ ለከፋ ረሃብ ተጋልጣለች፡፡

ዓለማችን ባለፉት አስርት ዓመታት ካስተናገደችው ረሃብ የላቀ በየመን ላይ ተከስቷል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአካባቢው የሰፈረውን የሽብር ቡድን ለመዋጋት የተደራጀው ሳዑዲ መራሹ ጦር ሥራውን በአግባቡ ባለማከናወኑ ነው ይላል የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ፡፡

ጦሩ ለተሻለ ዓላማ የተቋቋመ ቢሆንም ግቡን እየመታ ባለመሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመናውያን ለችግር ተዳርገዋል ተብሏል፡፡

የመን ለተጋረጠባት ችግር እጃቸውን የዘረጉ አገራት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ለዜጎቿ እንዳይደርስ የባህር፣ የየብስ እና የአየር ላይ ትራንስፖርት አማራጮቿ፤ በአሸባሪነት የተፈረጁ ታጣቂዎችና ሰላም አስከባሪነት ተልዕኮ በተሰጠው ቡድን ተዘግተዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ደግሞ የመንግስታቱን ድርጅት ጨምሮ ከሌሎች አካላት የተገኙ ድጋፎች በበቂ ሁኔታ ሊደርሱ አልቻሉም ተብሏል፡፡

በተያዘው ሳምንት የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ቡድን በአካባቢው የነፍስ አድን ሥራቸውን ለማከናወን ተቸግረው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በአገሪቱ ከ900 ሺ በላይ ዜጎች በኮሌራ የተጠቁ ሲሆን እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አሁንም ለከፋ ረሃብ ተዳርገዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በጦርነቱ እና በአገሪቱ በተከሰተው ረሃብና ወረርሽኝ 9ሺ የሚጠጉ ንፁሃን ህይወታቸውን ሲያጡ 50 ሺ የሚሆኑት ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡  ከእነዚህ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የየመን ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ( ምንጭ: ቢቢሲ)