ጀርመን ለግብጽና ሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ መሸጧ ተመለከተ

ጀርመን በአዉሮፓዉያኑ የቀን ቀመር 2017 በ3ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ብቻ ከባለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወደ ግብፅ እና ሳውዲ አረቢያ የላከቻቸው የጦር መሳሪያ የአምስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ ።

ሮይተርስ የጀርመን መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ግብጽና ሳውዲአረቢያ በየመኑ ጦር ላይ በሰፊው መሳተፋቸው ለከፍተኛ  የጦር መሣሪያ ግዠው  ዋነኛ  መንስኤ  ነው ተብሏል ።   

የሀገሪቱ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ድርጊቱን በመተቸት ላይ ይገኛሉ፡፡ ካይሮ እና ሪያድ  ለመሳሪያዎቹ ጊዢ ለጀርመኑ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ የሚያወጡት ወጪም እንዲሁ በከፍተኛ ማሻቀቡ ተነግሯል፡፡

ቁጥሩን ይፋ ያደረጉት ደግሞ የግራ ክንፍ ፓርቲ ኃላፊ ስቴፋን ሊየቢች ናቸው፡፡ በተጋለጠዉ ማስረጃ መሰረትም ግብፅ ከጀርመን የ300 ሚሊዮን ዩሮ የጦር መሳሪያ በመግዛት ትመራለች፡፡

ቁጥሩ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ45 ሚሊየን ዩሮ የጀርመን የጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ሲነፃፀር ምን ያህል ጣራ የነካ መሆኑን ያስውረዳል፡፡ ሪያድ በበኩሏ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የጀርመን የጦር መሳሪያ ግዢዋ ከባለፈው ዓመት የ41 ሚሊዮን ዩሮ ወደ 148 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ብሏል፡፡

ዘገባዉ ጨምሮ እንደሚያስረዳው ጀርመን በዚህ አመት ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት እና ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ኔቶ ያቀረበችው የጦር መሣሪያ ሽያጭ በግማሽ አንሷል፡፡

ሀገሪቱ ከአውሮፓ ሀገራት እና ኔቶ ውጭ ላሉ ሀገራት ያቀረበችው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ግን በእጥፍ በማደግ ሽያጩ ከ871 ሚሊዮን ዩሮ በመድረስ ከ1 ቢሊዮን ዶላር መሻገሩን ያስረዳል ዘገባው፡፡

ዘገባው ለእያንዳንዱ ሀገራት የተሸጡትን የጦር መሳሪያ አይነቶች ከመዘርዘር ግን ተቆጥቧል፡፡ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር መንግስት ይፋ ያደረገውን መረጃ በዋቢነት በማንሳት 4 የቦቴ ፓትሮል እና 110 የመከላከያ ሠራዊት መጫኛ ተሸከርካሪዎች በሽያጩ መካተታቸው እንዳልቀረ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡

ድርጊቱን ክፉኛ የተቹት የጀርመን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግስታቸው በየመን ጦርነት ነዳጅ እያርከፈከፈ ነው በማለት ወቅሷል፡፡ በተለይ ደግሞ ለግብጽ እና ሳውዲ አረቢያ የተሸጡ የጦር መሳሪያ በገፍ መጨመሩ ሊተች የሚገባ ነው ብሏል የግራ ዘመሙ ፖሊቲከኛ ሊየቢች፡፡

ግብጽ እና ሳውዲ አረቢያ ኃላፊነት ለጎደለው የየመን ጦርነታቸው መልስ የላቸውም፡፡ ጀርመን በምክንያት አልባው የየመን ጦርነት ላይ ለሚሳተፉ ሀገራት የጦር መሳሪያውን ስለመሸጡ ማጤን ይጠበቅባታል፡፡

 ድርጊቱ ጀርመን በእርሰ በእርስ ጦርነት የሚትታመሰውን ሀገር ለመምታት የሚደረገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ መርህ የሚጻረርም እንደመሆኑ ሊቆም የሚገባው ነዉ ብሏል ሊየቢች ለደችላንድፋንክ ብሮድካስተር በሰጡት ቃለ ምልልስ፡፡

የግሪን ፓርቲ ተባባሪ ሊቀ መንበር ሲሞነ ፒተር በቲዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክትም ዲርጊቱ ሰብአዊነት የጎደለዉ እና ህግን የጣሰ በማለት የሊየቢችን ሃሳብ ደግፏል፡፡ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስተር ግን የግብጽ እና የግብፅ እና የሳውዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተከላክሏል፡፡

መንግስት ለሽያጭ የማይቀርቡ የጦር መሳሪያዎችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቷል ሲሉም ለዶቼ ዌሌ ተናግሯል፡፡

ግሪን ፓርቲ እና ሌሎች ተቃዋሚ የጀርመን የፖሊቲካ ፓርቲዎች ግን ጀርመን በወረቀት ላይ ያሰፈረችአቸውን ህግጋት ልታከብር ይገባል ሲሉ ጉዳዩን ተችለውታል፡፡  ከ2 አመታት በፊት የጀርመን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሲግማር ጋብሪኤል ጀርመን ለአረቡ ዓለም የሚትሸጣቸውን የጦር መሳሪያዎችን ታጤናለች በማለት የሳውዲን ጥያቄ ማዘግየታቸው ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ያሉት ግን ራስን ለመከላከል የሚሸጥ የጦር መሳሪያ ከማቅረብ ጀርመን አትቆጠብም፡፡

እንደ ጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ በርሊን በ2016 ብቻ ለሪያድ 530 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣውን የጦር መሳሪያ አቅርባለች፡፡ ሄሊኮብተር እና ጄቶች ደግሞ በሽያጩ ከተካተቱ የጦር መሳሪያዎች ነው፡፡

ሳውድ አረቢያ ከመጋቢት 2015 ጀምሮ በየመን የሁቲ አማፅያን ለመምታት በሚደረገው የጦር ዘመቻ ላይ መሆኗን ትገልፃለች፡፡ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም ግን በአካባቢው የንፁሃን ዜጎች ሞት መበራከቱን ተከትለዉ ሪያድን በተደጋጋሚ ይተቻል፡፡( ምንጭ:ሮይተርስ)