ቆሻሻነቱ የታደሰለት ሀብት

‹‹ቴክኖሎጂ ባለህበት ምስጋና ይድረስህ!››ብንለው አባባሉ ሲተነተን አሳማኝ ሆኖ ስለሚገኝ ተገቢ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል እላለሁ፡፡ወደ ቀደሙት ጊዜያት ፊታችንን ስናዞር በተለይ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩት እንስቶች የኑሮን ቀዳዳ ለመድፈን የሚኳትኑበት ህይወት እጅጉን ያማርራል፡፡ማዕድ አቅርቦ ለመብላት የሆዳቸው ፍላጎት ሲያይል የማብሰያው ጉዳይ እጅጉን ውጣ ውረድ የበዛበት ነው፡፡ ዱር ሄዶ ማገዶ ለመልቀም አጋምና ጋሬጣ የተባሉት የእሾህ ዝርያዎች ከለበሱት አልባሳት ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቁ በልቀቀኝ አልለቅም ሙግት እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ማን ይገላግላቸዋል፡፡ በእግር ተረከዛቸው ስርለስር እሾህ ዘልቆ ሲገባ፣ በስራ ጫና እንደ ሞረድ በሚሻክሩት መዳፎቻቸው ሲሰገሰግ ለስቃይ ሲዳርጋቸው ማስተዋል የተለመደ ነበር፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ቀያቸውን አቋርጠው ከሚፈሱት ወንዞች ረጅም ርቀት ተጉዘው ጥቂት በመጨለፍ ተሸክመው ያመጡትን ውሃ ለመጠጥና ለሌሎች አገልግሎቶች ለማዋል ደፋቀና ሲሉ በርካታ ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡ውሃ ለመጠጣት የፈለገ ሰው የእነሱን ድካም ሲያስብ አፉን ደም ደም ይለዋል፡፡ በዚህ የአኗኗር ዘይቤ ማለፍ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡

        ለማገዶነት እንዲያገለግሉ የተፈረደባቸው ዛፎች ጠላት ይመስል እየታደኑ በመጥረቢያ ሲጨፈጨፉ ተንኮታኩተው መውደቅ እንጂ የማን ያለህ ይላሉ፣ ከሰሉን ለማክሰል ሲባል ከሰል አክሳዩ እንደ መልካም ጠላ ጠማቂ እንስራ በጭስ ሲታጠን በራሱ ላይ የሚያደርሰው የጤና እክል ደግሞ ይብሱን ጉዳቱን የከፋ ያደርግበታል፡፡

ከሰሉ ሲሸጥም ቢሆን ሻጩ ከከተሜው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ለነገሩ አይፈረድበትም፤ ገዢውም ቢሆን የገዛበትን ገንዘብ መወደድ አስቦ ማማረር ተገቢ አይደለም፡፡ የነበረውን ውጣ ውረድ በማሰብ መጽናናቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ሌላ አማራጭ እስካልተገኘ ድረስ በገንዘቡ በገዛው ከሰል ከጭስ ጋር ታግሎ አብስሎ መብላት ግድ ይሆንበታል፡፡

የሆነው ሆኖ በዚህ ሁሉ የኑሮ ውጣ ውረድ አልፈው በለቀሙት እንጨት ምግባቸውን አብስለው የቤተሰቦቻቸውን የሚጮህ ጉሮሮ ዘግተው የሚያድሩት የማህበረሰብ አባላት ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም፡፡

ዛሬ ግን ከዚያ አስከፊ የኑሮ ውጣ ውረድ ተላቀው ከፊት ለፊታቸው የተጋረጠባቸውን  የኑሮ ጫና ገሸሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ መንግስት አበረታች ስራዎችን በመስራት ላይ ነው። አሁን ለዚህ ጉዳይ አማራጭ ተገኝቷል፡

ከውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስልጣንና ተግባራት መካከል  የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ማስፋፋትና ማሳደግ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ የሶላርና የባዮጋዝ ቴክኖሎጂዎች ‹‹አማራጭ ኢነርጂ!›› ተብለዋል፡፡ የችግሩ ሰለባ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎች መታደግ በማስቻላቸው እፎይታን አስገኝተዋል፡፡

በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ የሚመደበው ባዮጋዝ ከተክሎች ቁሳዊ ፈሳሽ፣ ከከብቶች እበት፣ ከሰዎች አይነምድር፣ ከምግብ ተረፈ ምርትና ከመሳሰሉት በታመቀ የአየር ውህደት የሚመረት ንጹህ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

የባዮ ጋዝ ተግባር በሂደት ላይ

Horizontal Scroll: የባዮ ጋዝ ተግባር በሂደት ላይ 

የታዳሽ አማራጭ ኢነርጂ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ  የገጠር ኢነርጂ ማስተባበሪያ ማዕከል እ.ኤ.አ በ2009 ብሄራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም ማስተባበሪያ አቋቁሟል፡፡ ሁለተኛው የፕሮግራሙ ምዕራፍ የተጀመረው ደግሞ ሰኔ 2014 ሲሆን ሐምሌ 2022 እ.ኤ.አ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ፕሮግራም የተቋቋመበት ዓብይ ምክንያት ታዳሽ አማራጭ ኢነርጂን በማስፋፋት የሃገርና የህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማገዝ ታስቦ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ቴክኖሎጂ ኦርጋኒክ ማዳበሪያ በማምረት የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ጥቅሙ በኢነርጂ ምንጭነት ብቻ የሚወሰን ስላልሆነ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው፡፡

በመሆኑም ብሄራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራሙ በስምንት ክልሎች እንዲከናወን ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች በሚገኙ ሁለት መቶ ሃምሳ/250/ በሚጠጉ ወረዳዎች ላይ ፕሮጀክቱ ትኩረት አድርጓል፡፡

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የህዝብ ግኝኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የካቲት 2009 ዓ.ም ባሳተመው መጽሄት ብሄራዊ የባዮጋዝ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በማቋቋም በአገር አቀፍ ደረጃ መርሃ ግብር ወጥቶለት እንደ እ.ኤ.አ በ2009ዓ.ም በአራት ክልሎች በትግራይ፣በአማራ፣በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት ለአራቱ ክልሎች ቅድሚያ የሰጠበት ምክንያት ደግሞ ክልሎቹ በቂ ውሃ በቀላሉ ስለሚያገኙ፣ ካላቸው ከፍተኛ የከብት ሀብት፣ እንዲሁም ባብዛኛው በእነዚህ ክልሎች የሚኖሩት የማህበረሰብ ክፍሎች የአሰፋፈር ሁኔታ በጣም የተቀራረበ ስለሆነ ለፕሮግራሙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ መሆኑን ጽሁፉ ያትታል፡፡

መንግስት ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ስራውን እንዲያሳልጥ ፋይናንስ የአንበሳውን ሚና የሚጫወት መሆኑ አያጠራጥም፡፡ ይህንን ለመሸፈን ደግሞ ብቻውን የሚዘልቀው ይሆናል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ የህብረተሰቡ እና የአበዳሪ ተቋማት ድጋፍ ሲታከልበት ፕሮጀክቱ በታሰበለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለዚሁ ለብሄራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም የተያዘው ጠቅላላ በጀት 755ሚሊዮን ብር ሲሆን 8.2 ሚሊዮን ከሂቮስ በተገኘ እርዳታ ተሸፍኗል፡፡ በተጨማሪም 4.5 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በመንግስት ሊሸፈን እቅድ ተይዟል፡፡ እንዲሁም 20ሚሊዮን ዩሮ ከአውሮፓ ህብረት በተደረገ እርዳታ የተገኘ ሲሆን ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ በመንግስት እንዲሸፈን እቅድ ተይዟል፡፡

በዚህ መሰረት ከ2008 እስከ 2017እ.ኤ.አ አጋማሽ ድረስ ለባዮጋዝ ፕሮግራሙ ከተመደበው በጀት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው126 ሚሊዮን 365 ብር መሆኑን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የአማራጭ ኢነርጂ ዳይሬክቶሬት የኦዲት ሪፖርት ያሳያል፡፡  

በእቅዱ መሰረት 20,000 ባዮጋዞች በሂቮስ በሚደገፈው ፕሮጀክት የሚሰሩ ሲሆን 36,000 ባዮጋዞች ደግሞ በአውሮፓ ህብረት የሚሸፈን ይሆናል፡፡ እንደ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 56,000 የቤተሰብ የባዮጋዝ ሲስተሞችን በመገንባት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለሚችል ምትክ የለሽ የሃይል አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

 

ባዮጋዝ ጥ ብርሃን አገልግሎት

Horizontal Scroll: ባዮጋዝ ጥ ብርሃን አገልግሎት ትግበራው ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ እ.ኤ.አ 2017ድረስ 17,500 ባዮጋዞች በ17,500 ቤቶች ተተክለው 87,500 የሚሆኑ ነዋሪዎችን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ አፈጻጸሙም 74 በመቶ ደርሷል፡፡

ባዮ ጋዝ ለቤት ውስጥ ብርሃን አገልግሎት ሲውል

Rounded Rectangle: ባዮ ጋዝ ለቤት ውስጥ ብርሃን አገልግሎት ሲውል 

ቴክኖሎጂው አረንጓዴ ልማትን ከመታደግ አንጻር በተገነቡት ባዮጋዞች አማካኝነት 236,285 ቶን የሚሆን ማገዶ ከጭፍጨፋ እንዲድን ለማድረግ አስችሏል፡፡ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅ አኳያም 26,640 ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ለምነቱ እንዲዳብር አስችሏል፡፡

በዚህ ተግባር ስራና ሰራተኛ እጅጉን ተቆራኝተዋል፡፡ በበርካታ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎች  ለሃገርና ለወገን የሚተርፍ ተግባር ሲፈጽሙ ስናስተውል እውቀታቸው የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ አይቀርም፡፡ ባለሙያዎች ውስጣቸው የፈቀደው ሞያ በእውቀትና በክህሎት ሲታገዝ እጃቸውን ስመው የሚቀጥሯቸው ተቋማት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህ የባዮ ጋዝ ፕሮጀክቶች ሙያና ሙያተኛውን እጅና ጓንት አድርገው አገናኝተዋቸዋል፡፡ 1,110 ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ እድል አስገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 30% የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ በተገነቡት ባዮጋዞች 43,750 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ደግሞ ይበል የሚያስብል ተግባር ነው፡፡

 

ሴቶች በባዮጋዝ ተጠቅመ ምግብ   ሲያበስሉ    

Wave: ሴቶች በባዮጋዝ ተጠቅመ ምግብ   ሲያበስሉ     ማንኛውም ስራ ሲከናወን ችግር ወይም ተግዳሮት ጠፍቶ አያውቅም፡፡ይሁንና ቶሎ ተስፋ የሚቆርጥ እንዳለ ሁሉ ችግሩን ተቋቁሞ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚያሰላስለው የሰው ልጆች አዕምሮ ቀላል አይደለም፡፡ እናም መንግስት የተለያዩ እቅዶችን ያቅዳል፤ እቅዱን ለማስፈጸም የሚጀመሩ ስራዎች ውስብስብ ችግሮችን አዝለው ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችንም ከዳር ለማድረስ ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነው አይጠብቁም፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ እጥረት፣የግል አልሚው ተሳትፎ ቁጥር አናሳ መሆን፣ የብድር አገልግሎት ለማግኘት ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠርና በግብዓትነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በቀላሉ አለመገኘት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ባዮጋዝን ለማዳረስ ሲባል የሚከሰተውን የገንዘብ ጫና ለመቀነስ ከአለም ባንክ የተገኘውን ፋይናንስ ለተጠቃሚዎች በብድር መልኩ ማቅረብ ሌላው ዘዴ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በብድርና ቁጠባ ተቋማት አማካኝነት ለማሰራጨት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለማገኘቱ በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎች ይገለጻል፡፡

ሌላው  የቴክኖሎጂው ገበያ መር መሆንና የግል አልሚዎች ለባዮጋዝ ልማት  የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ለዚህ ዘርፍ ትልቅ ሚና ቢኖረውም ከሌሎች ግንባታዎች ጋር ሲነጻጸር ግን የግሉ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ አነስተኛ መሆኑም በስራው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ ይገለጻል፡፡

ለባዮጋዝ ግንባታ ከሚያስፈልጉ አቅርቦቶች መካከል ከፊሎቹ በአገር ውስጥ የማይመረቱና ከውጭ የሚገቡት ደግሞ ዋጋቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የመለዋወጫ አቅርቦቱ አለመሟላት በቴክኖሎጂው መስፋፋት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ከብድር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመሆን ብድር በማመቻቸት የባዮጋዝ አቅርቦቱ እንዲያድግና አልሚዎች ወደ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ለባዮጋዝ ገንቢዎች ክፍያ እንዲስተካከል በማድረግ ቴክኖሎጂው ገበያ መር እንዲሆን ማድረግ ደግሞ ሌላው የችግር መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡

ቆሻሻ አስጸያፊ ነገር እንደመሆኑ መጠን ሁሉም እንደ ስሙ ያንቋሽሸዋል፡፡ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ራቅ አድርጎ ለመጣል ሲጣደፉ ይስተዋል፡፡ መንግስትም ቢሆን የሰው ሃይል የታከለበት የቆሻሻ ማንሻ ቁሳቁስ በማቅረብ ቆሻሻን ህብረተሰቡ ከሚኖርበት አካባቢ ራቅ አድርጎ ያስወግዳል፡፡

አሁን ይህ ጉዳይ ሊያበቃለት ጊዜው ተቃርቧል፡፡ ቴክኖሎጂ የተመሰገነ ይሁንና ቆሻሻን በማደስ ወደ ሃይል መቀየር ተችሏል፡፡ በከሰል ጭስ ምክንያት ተማረው የሚጨናበሱ ዓይኖች እንደ ንጋት ከዋክብት ማብራት ይጀምራሉ፤ ማገዶ ፍለጋ ዱር ለዱር በመንከራተት ማገናዘብ ለተሳናቸው ግለሰቦች ማንነታቸውን አሳልፈዉ የሚሰጡ ሴት እህቶቻችን እፎይታን ያገኛሉ፤ ለከሰል ግዢ የሚወጣ ወጪ እንደ ጠላት ገንዘብ በከንቱ አይወረወርም፡፡ ዛፎች እየተከተከቱ ሲወድቁ ሮሮ ማሰማታቸውን ሲያቆሙ አረንጓዴ ልማት እውን ይሆናል፡፡ ከብት አርቢው የከብቶችን እበት ለባዮጋዝ በማዋል ተረፈ ምርቱን ለመሬት ማዳበሪያነት ሲጠቀምበት ስናይ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ!›› ማለት ይህ ነው፡፡ ታዳሽ አማራጭ ኢነርጂ በርካታ ትሩፋቶች አስገኝቷል፡፡

ሀገራችን በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፉ ከታዳሽ ሃይል ምንጭ ለመጠቀም የሚያስችል ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ይታመናል፡፡ ይህንን ሃብት በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል ተግቶ መስራት እንደሚገባ ሁላችንን የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ ሃብቱንም በአግባቡ ለመጠቀም ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የአማራጭ ኢነርጂ ምንጮችን በማልማትና ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት በዘርፉ የተሰማሩ የግልና መንግስታዊ የሆኑ ተቋማት ጥረት ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም፡፡

ምስጋና

መረጃውን በመስጠት ለተባበሩን ለውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የባዮጋዝ ፕሮግራም ሞኒተሪንግ ኢቫሉዌሽን ኦፊሰር አቶ ከተማ አድማሱ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡