ሩሲያ አሜሪካን አስጠነቀቀች

አሜሪካ ከጃፓንና ደቡብ ኮርያ ጋር የጀመረችውን ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎ ሩሲያ  አሜሪካንን  አስጠነቀቀች ።     

ሀገሪቱ አሜሪካ ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር የጀመረችው ወታደራዊ ልምምድ የቀጠናውን ሰላም የሚያደፈርስ ስትል ነው በወታደራዊ ኃይል ዋና አዛዥ ቬላሪ ጌራሲሞቭ በኩል ማስጠንቀቂያዉን ያስተላለፈችው፡፡

የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ዋና አዛዥ ጀነራል ቬላሪ ጌራሲሞቭ  ጃፓን፣ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያን ለማጥቃት ሲሉ የፈጠሩት የወታደራዊ ሽርክና እና የጦር ልምምዱንም መጀመራቸው በኮሪያ ልሳነ ምድር የነበረውን ውጥረት የሚያባብስ ነው ሲሉ ሀገራቱን ወቅሰዋል፡፡

ድርጊቱ የማታ ማታ ለመቆጣጠር የሚከብድ፣ ስሜታዊነት የሚፈጥር እና  የቀጠናውን ሰላም ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው ብለዋል አዛዡ ፡፡ ጌራሲሞቭ ይህን ያሉት ከጃፓኑ የመከላከያ ሚኒስትር እሱኖሪ ኦኖዴራ ጋር በቶኪዮ ባደረጉት ውይይት ሲሆን ይህ በሰሜን ኮሪያ ዙሪያ የሚደረገው ወታደራዊ ልምምዱ በቀጠናው ሰላምን ለማደፍረስ ትልቅ መንስኤ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት፡፡ 

አሜሪካ በያዝነው ሳምንት ከሁለቱ የኢሲያ አህጉር አጋሮቿ ከሆኑት ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ለመጀመር ዝግጅቷን ያጠናቀቀችበት መርሃ ግብር ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ወደ ቀጠናው ለማጓጓዝ የሚደረገውንም ሂደት የሚያካትት ስለመሆኑ እየተዘገበ ይገኛል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በቀጠናው ሚሳኤሎችን የመጫን እና የወታደራዊ ልምምድ የመጀመሩን ድርጊት ሀገራቱ በሀገሬ ላይ ጦርነት የመክፈታቸው ጅማሮ አድርጌ እመለከተዋለሁ ወደ ሚል ትርጓሜ በመውሰድ ላይ ነች፡፡    

ሀገሪቷ የሶስቱን ሀገራት ወታደራዊ ጥምረት ሰሜን ኮርያን ለመውረር የሚደረግ ሴራ ስትልም ሀገራቱን በተደጋጋሚ ትወነጀላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚሳኤል ፕሮግራሞቼን በሥራ ላይ በማዋል ለዩ ኤስ አፀፋውን ለመመለስ እገደዳለሁ ትላለች ፕዮንግያንግ፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በሙከራ ላይ ያዋለችው የቅርብ ጊዜዉ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሏ እስከ የአሜሪካ ምድር ርቆ መጓዝ እንደሚችል ማረጋገቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነዉ፡፡ ቻይና በበኩሏ ዋሽንግተን እና ፕዮንግያንግ የጀመሩትን የቃላት ጦርነት እና የወታደራዊ ልምምዱን በማቆም ለሰላም መስራት አለባቸው ስትል በተደጋጋሚ ጥሪ ስታቀርብ ተስተውላለች፡፡ 

ስለ የሶስቱ ሀገራት በቀጠናው የወታደራዊ ልምምድ መጀመር በቤጂንግ የተጠየቁት የቻይና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ በበኩላቸው ፥ ውጤቱ የማያምር ድርጊት ሲሉ ገልፀውታል፡፡

እናም አሉ ሚስተር ሉ፤ በወታደራዊ ልምምዱ እየተሳተፉ ያሉት ሁሉም ሀገራት የተባበሩት በመንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያስቀመጠውን የመፍትሄ አቅጣጫ በትክክል በመከተል ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ሲሉ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡  

ሩሲያ የክሬሚያን ግዛት ከዩክሬን ከነጠቀች በኋላ የጃፓን እና ሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትሮች ተገናኝተው ሲወያዩ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ የሚስቴር ጌራሲሞቭ የቶኪዮ ጉብኝት ሀገራቱ ለሁሉም ስለሚበጀው ነገር ተወያይቷል፡፡     

ሩሲያ እና ጃፓን የሶቪየት ህብረት ወታደራዊ ሀይል ከ2ኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ የሴሜናዊ ጃፓን ሆካሂዶ አራቱን ደሴቶች መቆጣጠሯን ተከትሎ እንደተቃቃሩ ናቸዉ፡፡ ይህን ተከትሎም ጃፓን ግጭቱ እስኪፈታ ድረስ ከሪሲያ ጋር የትኛውንም የሰላም ስምምነት ሳታረግ መቆየቷ ይታወቃል፡፡

ጌራሲሞቭ ግን በጉብኝታቸው የጃፓን የራስ መከላከያ ኃይል ዋና አዛዥ ካሱቶሺ ካዋኖንም አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡

የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ የቻይና እና የሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በቤጂን መጀመር ሁለቱ ሀገራት ራሳቸውን ከሚሳኤል አደጋ ለመከላከል የላቀ ትርጉም እንደሚኖረው  ገልፀዋል፡፡

ቻይና እና ሩሲያ አሜሪካ በደቡብ ኮርያ ከፍታ ቦታዎች እያደረገች ያለችውን የጦርነት መሰናድኦ ይቃወማሉ፡፡ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ይህን የምናደርገዉ የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል በቀጠናዉ የሚያስከትለዉን ስጋት በመፍራት ነዉ ይላሉ፡፡( ምንጭ:ሮይተርስና አልጀዚራ )