ቱርክ የሶሪያ አማፂያንን ለማጥቃት የኬሚካል የጦር መሳሪያ አልተጠቀምኩም ብላለች

ቱርክ የሶሪያ አማፂያንን ለማጥቃት የኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቅማለች መባሉን ውድቅ አደርጋለች፡፡

በሶሪያ የኩርድ YPG ታጣቂዎች ላይ ከአንድ ወር በፊት ቱርክ በተከፈተችው ጥቃት በርካቶች ለሞት ቁጥራቸው ያየሉ ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ንፁሐን ዜጎች ይገኙበታል፡፡ በወቅቱ አንካራ ያደረሰችው ጥቃት በዓለማቀፍ ደረጃ የተከለከለ የኬሚካል መሳሪያን ተጠቅማለች ሲሉ ሌሎች አገራት ሲከሷት ነበር፡፡

በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ንፁሐን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ለሞትና ለአተነፋፈስ ችግር መጋለጣቸውም የሚታወስ ሲሆን፤ ለእነዚህ ምንዱባን ጉዳት ቱርክ መጠየቅ አለባት ሲሉም በሌላኛው ወገን በሶሪያ የአሸባሪ ቡድኖች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አገራት ይወነጅላሉ፡፡

የቱርኩ ፕሬዚደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አማካሪ የሆኑት ያሲን አክታይ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት ከሆነ፤ አገራቸው የተከለከለውን የኬሚካል የጦር መሳሪያ በሶሪያ ምድር ላይ አልተጠቀመችም፡፡

ይህንን አይነት ድርጊት ቱርክ በአያሌው የምታወግዘው ሆኖ ሳለ እንዴት ትጠቀመዋለች ሲሉም አማካሪው ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት የነበረውን ጥቃት ሲያጣራ የነበረው በዩናይትድ ኪንግደም የሚታገዘው የሃኪሞች እና የምርመራ ቡድን ቱርክ የኬሚካል ጥቃት አድርሳለች ሲል የምርመራውን ውጤት ይፋ በማድረጉ የዓለም መንግስታት አንካራን ሲወቅሷት ነበር፡፡

በሶሪያ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች ባደረጉት ምርመራ ደግሞ ጥቃቱ በንፁሃን ላይ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የፈጠረባቸው ቢሆንም የኬሚካል የጦር መሳሪያ ይሁን አይሁን ግን አልለየሁም ብሏል፡፡

በዚህም አገራት ለሁለት ተከፍለው በጥቃቱ ዙሪያ ሲወነጃጀሉ እንደነበርም ይነገራል፡፡

በሶሪያ ከአፍሪን ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ 30 ኪሎ ሜትር የምትርቀው አል-ሼክ ሀዲድ ግዛት ውስጥ በኩርድ የYPG ታጣዎች ላይ በተፈፀመው ጥቃት ከ1 ሺህ 600 በላይ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት የተገደሉ ሲሆን 32 የመንግስት ታጣቂዎች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን የመንደሩ ነዋሪዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳትን አስተናግደዋል፡፡

እናቶችና ህፃናትም የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙ ናቸው፡፡

የሶሪያን መንግስት እንደሚያግዝ የሚያምነው የቱርክ ወታደራዊ ሀይል ለእነዚህ ንፁሃን ጉዳት ተጠያቂ ሲሆን ቢቆይም፤ ውንጀላውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

በሶሪያ ያሉ አሸባሪዎችን እናጠፋለን የሚሉት ሩሲያ እና አሜሪካ አንካራን በአንድ ወገን ሆነው ሲተቹ ቢከርሙም አሜሪካ አሁን ከቱርክ ወገን መሆኗን ካሰታወቀች በኋላ ቱርክ ወቀሳውን ማጣጣሏ የቱርክን ሀሳብ ውሃ እንዳያነሳ ያድርገዋል፡፡- /አልጅዚራ/