አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የጦር ኃይሏን ልታስወጣ መሆኑ ተገለጸ

አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የጦር ኃይሏን ልታስወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ወደ 2ሺ የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን ከሶሪያ እንዲወጡ ያዘዙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሁን ደግሞ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ከ7 ሺ በላይ ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን ሊያስወጡ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

ስማቸው ያልተጠቀሰ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በአፍጋኒስታን ከሚገኘው የአሜሪካ ጦር ውስጥ ግማሽ የሚሆነው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል፡፡

ባለስልጣናቱ ይህንን ይበሉ እንጂ የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስቴር ግን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን ምርጫው አድርጓል፡፡

የዋሽንግተን ፖስቱ ዘገባ እንደሚያመላክተው ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የነጩ ቤተመንግስት ሃገር አቀፍ የደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተንን ጨምሮ በሌሎችም ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የፓርላማ አባላት ዘንድ ነቀፌታ ገጥሞታል፡፡

የሪፐብሊካኑ ሴናተር ሊንዲሴይ ግርሀም ይህንን የአሜሪካን የጦር ኃይሏን ከአፍጋኒስታን የማስወጣት ውሳኔ የታሊባን በአፍጋኒስታን ግዛቱን እያስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ትልቅ  ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ስትራቴጂ እንደሆነ በቲውተር  ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

የአሜሪካንን ከአፍጋኒስታን መውጣት ለሚደግፉ ወገኖች ይህ ውሳኔ አሜሪካ በሰው ሀገር አፈር ላይ ለረጅም ጊዜ እንድትቆይ ምክንያት ለሆናት እና ከ2 ሺህ 300 በላይ ወታደሮቿን ህይወት ለቀጠፈባት ግጭት መቋጫ ማበጀቷን አመላካች ሲሆን ለአብዛኞቸች ግን ይህ ውሳኔ ግዛቱን እያስፋፋ ላለው ታሊባን ትልቅ እድልና አፍጋኒስታንን ወደ ጦርነት አውድማ ሊቀይራት ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገልጿል፡፡

ይህ ዜና የተሰማው አሜሪካ በሶሪያ የሚገኘውን ወታደሮቿን ሙለ በሙሉ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ካዘዘች ከ1 ቀን በኋላ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው መከላከያ ሚንስትር ጆን ማቲስም ከኃላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተነግሯል፡፡

ማቲስ ከስልጣናቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡት አሜሪካ ወታደሮቿን ከሶሪያ ማስወጣቷን ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች ቢጠቁሙም የመልቀቂያ ደብዳቤው ላይ ግን ማቲስ በምክንያትነት ያስቀመጡት ጉዳይ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያላቸውን የሓሳብ ልዩነት መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከመመረጣቸው በፊት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አሜሪካውያኑን ከመረጣችሁኝ በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የአሜሪካንን የጦር ኃይል አስወጣለሁ ቢሉም ባለፈው አመት ግን ታሊባን እንደገና ማንሰራራቱን ተከትሎ ሀገሪቷን ከመፈራረስ ለመታደግ ወታደሮቻቸውን እዛው ለማቆየት መወሰናቸውን አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡

እ.ኤ.አ በ2001 መስከረም 11 በአሜሪካ ፔንታጎን ህንጻ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ አፍጋኒስታን ማስገባቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አሜሪካ ለሽብር ጥቃቱ ተጠያቂ ነው ያለችውን የአልቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢላደን  አፍጋኒስታንን ሲያስተዳደር የነበረው ታሊባን አሳልፎ እንዲሰጣት ጥያቄ ብታቀርብም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ ቢላደንን ለመያዝና ታሊባንን ከሥልጣን ለማውረድ የጦርነት ዘመቻ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ እና ዋሽንግተን ፖስት)