ፕሬዚዳንት ትራምፕ በከፊል ተዘግተው የነበሩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች እንዲከፈቱ ተስማሙ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በከፊል ተዘግተው የነበሩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ለተወሰነ ጊዜ እንዲከፈቱ ተስማሙ።

ፕሬዚዳንቱ ላለፉት 35 ቀናት ተግባራዊ የተደረገው የፌደራል መስሪያ ቤቶችን የመዝጋት ሂደት ለሶስት ሳምንታት እንዲቋረጥ ተስማምተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን ከሜክሲኮ በሚያዋስነው ድንበር ለማስገንባት ላቀደው የአጥር ግንብ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት የተወሰኑ የፌደራል መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፕሬዚዳንቱም ለአጥር ግንቡ ማስገንቢያ የሚሆነው 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ካልተገኘ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን የመዝጋቱ ሂደት ይቀጥላል ሲሉም ተደምጠው ነበር።

ይሁን እንጅ ትናንት የሃገሪቱ ኮንግረስ አባላት ባደረጉት ስብሰባ የትራምፕ አስተዳደር በከፊል የመዝጋት ሂደቱ ለሶስት ሳምንታት እንዲቋረጥ የተስማማ ሲሆን ይህ መሆኑ ለዴሞክራቶች ትልቅ ድል ነው ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሁን ላይ እንዲቋረጥ የተስማሙት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመዝጋት ሂደት ከሶስት ሳምንታት በኋላ በቀጣዩ የፈረንጆች የካቲት ወር አጋማሽ ላይ ዳግም ይጀመራል ብለዋል።

ይህ የማይሆንና የማይሳካ ከሆነ ግን ለአጥር ግንቡ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት በአሜሪካ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉም እየተባለ ነው።

ከወር በላይ በዘለቀው የትራምፕ የመንግስት መስሪያ ቤት የመዝጋት እርምጃ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች ተጎጂ ሆነዋል።

በርካቶችም በአሜሪካ ታሪክ ረጅም የተባለውን እርምጃ በማውገዝ ትራምፕን ኮንነዋል። (ምንጭ፦ሮይተርስ)