ትራምፕ እና ኪም የቬትናሙን ዉይይት የጋራ ስምምነት ሳይፈርሙ ተጠናቀቀ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጁንግ ኡን በቬይትናም ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

ሁለቱ መሪዎች ከስምንት ወራት በኋላ ነበር ለሁለተኛ ጊዜ በቬይትናሟ ሃኖይ ትናንት የተገናኙት።

በቬይትናም ባደረጉት ውይይትም ከተያዘለት ቀጠሮ ከሁለት ሰዓታት በፊት መጠናቀቁ ተገልጿል።

የውይይቱ መጠናቀቅ ተከትሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ውይይቱ ያለስምምነት ቢጠናቀቅም ፍሬያማ የሚባል ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በውይይቱ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ነገር ግን ስምምነቶችን መፈረም ያለመፈለጋቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ወቅት ሰሜን ኮርያ በአሜሪካ የተጣሉባትን ማዕቀቦች ሙሉ ለሙሉ እንዲነሱ ትፈልጋለችም ብለዋል።

በምላሹም ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር ማዕከሎቿን እንደምተዘጋ ማስታወቋን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰሜን ኮርያ በተጠየቀችው መሰረት ሁሉንም ማዕከሎቿን ለመዝጋት ያለመፈለጓን ጠቅሰው፥ በዚህም አሜሪካ ሀገሪቱ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንደማታነሳ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ የሰሜን ኮርያ አቻቸው አዲስ የኒውክሌር መሳሪያ ሙከራና የረጅም ርቀት ሚሳዔል እንደማይሞክሩ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመግለጫቸው አሁን የደረሱበትን ጉዳይ ከደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃ ኢን ጋር በቅርቡ እንደሚመክሩበት አስታውቀዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ውይይቱን ለመቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ ወደፊት ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተስፈኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጁንግ ኡን በበኩላቸው ስለቬትናሙ ውይይት እስከ አሁን ያሉት ነገር የለም ተብሏል። (ምንጭ፡-ቢቢሲና አልጀዚራ)