በጣሊያን በደረሰ ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር 247 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2008 (ዋኢማ)-በመካከለኛው ጣሊያን በደረሰ ከባድ ርዕደ መሬት ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቍጥር 247 መድረሱ ተነግሯል።

አሁንም በህይወት ያሉትን ሰዎች የማፈላለጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉም ታውቋል።

ቁጥራቸው 4 ሺህ 300 የሚደርሱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማፈላለጉን ስራ በከባባድ መሳሪያዎች በመታገዝ እያከናወኑ መሆኑም ታውቋል።

አሁንም በርካታ ሰዎች አማትሪስ፣ አኩሞሊ እና ፔስካላ ዴል ቶሮንቶ ተራራማ አካባቢ በርካቶች ከፍርስራሽ ስር እንዳሉ እየተነገረ ነው።

በርዕደ መሬቱ ትናንት ከዋና ከተማዋ ሮም በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አማትሪስ ከተማ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

የከተማዋ ከንቲባ ሰርጂዮ ፔሮዚ እንደተናገሩት የከተማዋ አብዛኛው ክፍል በርዕደ መሬቱ ፈራርሷል፡፡

የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በአደጋው በርካታ ህፃናት ተጎድተዋል ያሉ ሲሆን፥ አሁንም የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብሏል።

በዚህ ሳቢያም የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 2 የተለካው ርዕደ መሬት 10 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቆ ሰሜን ምስራቃዊ ሮምን አንቀጥቅጧል፡፡

ጣሊያን ከ7 ዓመታት በፊት ባጋጠማት ከባድ ርዕደ መሬት 309 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)