የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በስደተኞች ጉዳይ ከስምምነት ላይ ደረሱ

የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከእልህ አስጨራሽ ድርድርና ውይይት በኋላ በስደተኞች ጉዳይ ከስምምነት ላይ ደርሷል።

በቤልጅየም ብራስልስ የተሰበሰቡት የአውሮፓ መሪዎች 10 ሰዓታት የፈጀ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ነው ስምምነት ላይ የደረሱት።

አገራቱ በመጨረሻ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከስምምነት መድረሳቸውን የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

ጣሊያን ብዙ ስደተኞች በተለይም ከአፍሪካ ወደ ሀገሯ ባሕር አቋርጠው የሚገቡትን  በመቀበል ረገድ ሌሎች የህብረቱ አባላት የማያግዟት ከሆነ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውሳኔውን እንደምትቀለብስ ማስፈራሪያ ስታቀርብ ነበር።

ይሁንና አሁን አዲሱ ስምምነት የስደተኛ መቀበያ ማዕከላት በሁሉም የኅብረቱ አገራት እንዲቋቋም የሚያበረታታ ሲሆን አገራቱ ማዕከላቱን ለማቋቋም ባይገደዱም በፍቃደኝነት ላይ ተመሥርተው ግን ይህንኑ እንዲያደርጉ ስምምነቱ ያበረታታል ነው የተባለው፡፡

እነዚህ ወደፊት እንደሚቋቋሙ የተነገረላቸው የስደተኛ ማዕከላት ማን ወደ አገሩ መመለስ እንዳለበትና የትኛው ስደተኛ ከለላ ማግኘት እንዳለበት ከመወሰናቸውም ባሻገር የማጣራት ሥራውንም ያፋጥናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የ28 አገራት የኅብረቱ መሪዎች የስደተኛ ማዕከላትን ከማቋቋም በዘለለ ቱርክ፣ ሞሮኮና ሌሎች የሰሜን አፍሪካ አገራት ድንበሮቻቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ከስምምነት ደርሰዋል።

ጣሊያንና ግሪክ ሌሎች አገሮች የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ እገዛ እስካላደረጉ ድረስ ምንም ዓይነት ስምምነት ላለመፈረም ሲዝቱ ነበር።

የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል ከስብሰባው ቀደም ብሎ የስደተኞች ጉዳይ የህብረቱን ሕልውና የሚወስን ሊሆን እንደሚችል መጠቆማቸው የሚታወስ ነው።

የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ይህ የስደተኞች ጉዳይ ህብረቱን ቀውስ ውስጥ ሊከተው እንደሚችልም ሲተነብዩ ሰንብተዋል።

ሜርክል ወደ ስብሰባው ከመሄዳቸው በፊት ጀርመን ምንም ዓይነት ተጨማሪ ስደተኞችን እንዳይቀበሉ ግፊት ሲደረግባቸው ቆይቷል።

በኀብረቱ አገራት የተመዘገቡ ስደተኞች እያሉ ጀርመን አዳዲስ ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገዷን ሐሳብ እንድትተው በርካታ የኅብረቱ አገራት ሲወተውቱ እንደነበርም ነው የተመላከተው፡፡

የጀርመን ጣምራ መንግሥትን ከመሠረቱት ውስጥ አንዱ ሲኤስዩ ሜርከል በስደተኞች ላይ መጨከን ካልቻሉ ጥምረቱን እንደሚያፈርስ ሲዝት ነበር።

ፓርቲው ከጥምረቱ ከወጣ ደግሞ የሜርክል መንግሥት የምክር ቤቱን ብዙኃን መቀመጫን ስለሚያጣ አገሪቱን ለመምራት ይቸገራል።

የሕገወጥ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ጉዞ አሁን አሁን እየቀነሰ መምጣቱ ሲነገር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ወደ አውሮፓ የገቡ ሕገወጥ ስደተኞች የኅብረቱን አገራት መጠኑ ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ጥሏቸው ቆይቷል።

ከዚያ ወዲህ ግን ወደ ኅብረቱ አገራት የሚገቡ ከለላ ፈላጊዎች ቁጥራቸው በ96 በመቶ እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል።

በዚህ ወር ጣሊያን ለስደተኞች ድጋፍ የሚሰጠውንና የሚታደርገውን የጀርመን ግብረሰናይ መርከብ ወደ አገሯ እንዳይጠጋ ከከለከለች በኋላ በአገራት መካከል ከረር ያለ አለመግባባት መከሰቱ የሚታወስ ነው፡፡

በመጨረሻም ስደተኞችን የሚታደገው መርከብ በማልታ መልህቁን እንዲጥል ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ተደርሷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኖርዌይም የተወሰኑ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምታለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡