ሜላኒያ ትራምፕ በአፍሪካ የሚያደርጉትን የአምስት ቀናት ጉብኝት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ጀመሩ

የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በአፍሪካ የሚያደርጉትን የአምስት ቀናት ጉብኝት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ጀምረዋል፡፡

የቀዳማዊት እመቤቷ ጉብኝት በዋናነት የህጻናት ደህንነትን  ማበረታታት አላማው ያደረገ ሲሆን ጉብኝታቸውም በኬንያ፣ ማላዊ እና ግብፅ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በጋና አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በጋና አቻቸው አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በጋና ዋና ከተማ አክራ በሚገኘው ሆስፒታል ጉብኝት ያካሄዱት ቀዳማዊት እመቤት ሜሊና ትራምፕ በሆስፒታሉ በነበራቸው ቆይታ በሆስፒታሉ ለህጻናት የሚሰጡ ህክምናዎችን የተመለከቱ ሲሆን ለጨቅላ ህጻናት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበትን ክፍልም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ ለህጻናቱ እናቶችም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID)) የሚደገፈውንና በህፃናት ስነ-ምግብ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራውን ፕሮጀክት ተመልክተዋል።

ከዚህም ባሻገር ቢ ቤስት ኢንሼቲቭ በተሰኘ ድርጅታቸው ጤናን የሚያቃውሱ ነገሮችን በመግታት ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ያለመ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያስተዋውቁ ተገልጻል።

በአፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታም በኬንያ፣ ማላዊ እና ግብፅ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የጉብኝታቸው ዋነኛ ትኩረትም ጤናና ትምህርትን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪካ አገራት ህዝቦችን መዝለፋቸውን በብዙዎች ዘንድ ቅያሜን ፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የቀዳማዊት እመቤቷ የአንድ ሳምንት የአፍሪካ ጉብኝትም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ያለመ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

የቀዳማዊት እመቤቷ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ግሪሻም እንደገለጹት እመቤቷ አፍሪካን ለመጎብኘት ፍላጎት ያደረባቸው፤ ከዚህ ቀደም ወደ አፍሪካ ጉዞ አድርገው ስለማያውቁና አገራቱ የተለየ ባህልና ታሪክ ስላላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጉዞ ከመጀመራቸውም አስቀድሞ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በማላዊ የህፃናትን ትምህርት ለማሻሻል የሚያከናውነውን ፕሮግራም እንዴት ማስቀጠል እንዳለበነት ሲያስቡ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኬንያ በህፃናት ትምህርት፣ በዱር እንስሳት ጥበቃና በኤች አይ ቪ መከላከል ረገድ አሜሪካ ስታከናውን የቆየችውን ስራዎችም ጠቅሰዋል።

የጉብኝታቸው የመጨረሻ መዳረሻ በሆነችው ግብፅ በአገሪቱ የቱሪዝምና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን በተመለከቱ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። (ምንጭ፤ ሲጂቲኤን እና ቢቢሲ)