ሃሌሉያ ሆስፒታል በአንድ ሴት ላይ ባደረገው ቀዶ ጥገና 3 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ ማስወገዱን ገለጸ

በአዲስ አበባ የሚገኘው ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል የ32 ዓመት ወጣት ሴት ላይ ባከናወነው የቀዶ ህክምና በሳንባዋና በልቧ መካከል ተቀምጦ የነበረ 3 ኪሎ ግራም ክብደት የሚመዝን ዕጢ ማስወገድ መቻሉን አስታወቀ።

የሀሌሉያ ሆስፒታል እንደገለጸው ቀዶ ህክምናው ከሁለት ሰዓት በላይ ጊዜ ወስዷል ።

በሆስፒታሉ የሰመመን ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራእንደገለጹት፤ የሳንባ አካል ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ዕጢዎችን በቀዶ ህክምና ማስወገድ ይቻላል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ወጣቷ ላይ የተከሰተው ዕጢ በአይነቱ የተለየና በመጠንም ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

የዕጢው በመጠን ከፍ ያለ በመሆኑ የወጣቷን የቀኝ ሳንባ በመጫን አጨማዶትና ከጥቅም ውጪ አድርጎት እንደነበርና የልቧን መዋቅር አዛብቶ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ሳሙኤል በ15 ዓመታት የስራ ዘመናቸው እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል።(ኢዜአ)