የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ11 ዓመቷ ታዳጊ የቀረበላቸውን ማባበያ ውድቅ አደረጉ

የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኪንዳ አርደን መንግሥታቸው ድራገኖች ላይ ምርምር እንዲያደርግ 11 ዓመቷ ታዳጊ የቀረበላቸውን ጉቦ ሳይቀበሉ ቀሩ።

ጉቦውን በፖስታ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ የላከችው ታዳጊ ቪክቶሪያ እንደምትባል የተገለፀ ሲሆን፤ መግነጢሳዊ ኃይል ተጎናጽፋ ድራገኖችን ማሰልጠን ትፈልግ ነበር ተብሏል።

ታዳጊዋ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ሳይንሳዊ ፊልሞችን እንደምትከታተልና ለልዕለ ኃያላን ፍጡራን ልዩ ፍቅር እንዳላት ተነግሯል።

ይህች ታዳጊ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ በላከችው ደብዳቤ ውስጥ መንግሥታቸው በድራገኖችና በልዕለ ኃያላን ፍጥረታት ላይ ምርምር እንዲያደርግ እንደምትፈልግ ጠቅሳ፤ የኒው ዝላንድ 5 ዶላር (100 ብር ገደማ) ያስቀመጠች ሲሆን፤ ገንዘቡ ጉቦ ነው በሚል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ለታዳጊዋ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አርማ ባለበት ደብዳቤ ምላሽ የተሰጣት ሲሆን፤ አስተዳደራቸው "በአሁኑ ሰአት በድራገን ላይም ሆነ ልዩ ኃይል ባላቸው አካላት ላይ ምርምር እያደረገ አይደለም" ተብላለች።

"የላክሽልኝን ማባበያ ገንዘብ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አያይዤ የመለስኩልሽ ሲሆን፤ በመግነጢሳዊ ኃይል እና በድራገኖች ላይ የምታደርጊውን ፍለጋ እንድትቀጥይበት አበረታታሻለሁ" ብለዋታል።

በደብዳቤው ግርጌ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በእጅ ፅሑፍ ያሰፈሩት መልእክት እንዲህ ይነበባል።

"ማስታወሻ፡ እነዚያ ድራገኖችን ግን መከታተሌን አላቆምም። ሱፍ ይለብሳሉ እንዴ?"

የደብዳቤ ልውውጡ መጀመሪያ የተገኘው ሬዲት በተሰኘ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሆን፤ አንድ ግለሰብ ታናሽ እህቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ ጉቦ ለመስጠት መሞከሯን ገልጾ ጽፎ ነበር።

ቢቢሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ስለደብዳቤው እውነተኛነት ጠይቆ ትክክለኛነቱ ተረጋግጦለታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከታዳጊዎች የሚላክላቸውን ደብዳቤ ሲመልሱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከዚህ ቀደም የስምንት ዓመት ልጅ "አደገኛ የጦር መሣሪያዎች መታገድ አለባቸው ብዬ አስባለሁ" ብላ ለፃፈችላቸው ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሲመልሱ፤ "ከደብዳቤሽ መረዳት እንደቻልኩት ሩህሩህና ደግ ልብ ያለሽ ልጅ ነሽ" በማለት በቀሪው የሕይወት ዘመኗ በሙሉ መልካምነትን እንድታስቀድም መክረዋታል።