230 አመት ያስቆጠረ የድንጋይ ላይ ጽሑፍን ለሚተረጉም 2ሺ 250 ዶላር ሽልማት ተዘጋጀ

የፈረንሳይዋ ትንሽዬ ከተማ ፕላውጋስቴል በከተማዋ የሚገኘውና 230 አመት ዕድሜ ያስቆጠረ የድንጋይ ላይ ጽሑፍን ለሚተረጉም ማንኛውም ግለሰብ 2ሺ 250 ዶላር ለመሸለም መዘጋጀቷን ተነግሯል።   

ከጥቂት አመታት በፊት ግኝቱ የተነገረለት ይኸው የአለት ላይ ጽሑፍ በ20 መስመሮች በድንጋይ ላይ ተፅፎ የሚታይ ሲሆን እስካሁን ማንም እኔ ነኝ ባይ ተርጉሞ መልዕክቱን ጀባ ሊል አልቻለም ሲል ዘገባው አክሏል።

የሃገሪቷ ተመራማሪዎች ለበርካታ ጊዜያት የአለት ላይ ጽሑፉን ወደሚታወቅ ቋንቋ ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም ከንድፈ ሃሳብ የዘለለ አንዳች ጠብ የሚል ነገር ሊፈጥሩ አልቻሉም ብሏል ዘገባው።

የድንጋይ ላይ ጽሑፉ የጥንታውያን ብሪቶን ወይም ባስክ ሊሆን እንደሚችል በጥቂቶች መታመኑን የገለፀው መረጃው ጽሑፉን በአለቱ ላይ ያሰፈረው የጥንቱ ሰው ያልተማረ ወይም ከፊል መሀይም ሊሆን እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል።

‘ዘ ሻምፒዮን ሚስትሪ አት ፕላውጋስትል-ዳኦላስ’ በሚል ስያሜ በሚጠራው የድንጋይ ላይ ጽሑፉን የመተርጎም ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ በሃገሪቱ የስነ ቋንቋ እና የቅርስ ጥናት ጠበብቶች አማካይነት ጥሪው ቀርቦላቸዋል ሲል ነው ኦዲቲ ሴንትራል የዘገበው።

እንደ ዘገባውም በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በውድድሩ ለመካፈል የተመዘገቡ መሆኑን የገለፀው ድረ ገፁ በውድድሩ ለሚሳተፉትም የድንጋይ ላይ ጽሑፉ በድረገፅ እንደሚላክላቸው ነው የተገለፀው። የታሪክ አዋቂዎችን እና የቅርስ ተመራማሪዎችን ጋብዘው የድንጋይ ላይ ጽሑፉን ሲያስጠኑ መክረማቸውን የገለፁት የከተማዋ ከንቲባ ዶሚኒክ ካፕ ማናቸውም ከአለት ላይ ጽሑፉ ጋር የተያያዘውን ታሪክ ሊነግሯቸው እንዳልቻሉና ዕድሉንም በየትኛውም የአለማችን ክፍል ለሚኖረው ህዝብ መስጠታቸውን ተናግረዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ድረገፅ ዘግቧል።