የኬንያ አየር መንገድ ከኪሳራ ለማገገም የሚያስችለውን ዕቅድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ

የኬንያ አየር መንገድ ከደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ለማገገም የሚያስችለውንና ያለበትን የ2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመክፈል የሚረዳውን እቅድ አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ባለአክሲዎኖች የሆኑት የኬንያ መንግስትና 11 የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ያለባቸውን ብድር ወደ አክሲዬን በመቀየር ለመሸጥና ከደረሰባቸው የገንዘብ ፍሰት ጫና ለማገገም እየጣሩ ነው ተብሏል፡፡  

የአየር መንገዱን የግብይት ሁኔታ ሲያማክር የቆየውና የድርጅቱ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ቡቪ ጉንዜ ድርጅቱ ያለበትን የ2 ቢሊዮን ዶላር እዳን ለመክፈል የሚያስችል ዳግም መውቅር ነው፤እናም የንግድ ሥራውን እንደገና ለመቀልበስ ትንሽ ጊዜ ይሰጠናል ሲል ተናግሯል፡፡

አየር መንግዱ ዳግም ለመቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የኬንያ መንግስትም በበኩሉ በ10 ዓመት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ የ750 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቶታል፡፡

የአየር መንገዱ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ነው የተባለለትን የ26 ቢሊዮን ሽልንግ ወይም 251 ሚሊዬን ብር አመታዊ ኪሳራ በፈረንጆቹ 2016 ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ለዚህ ኪሳራ ደግሞ የተጓዦቹ ቁጥር መቅዛቀዝና ድርጅቱ በከፍተኛ ዋጋ አዳዲስ አውሮፕላኖችን መግዛቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ 

ድርጅቱ እስከ መጋቢት ባለው በአንድ የበጀት አመት ያስገባውና የወጣው ወጪ ሲሰላ በ45 ሚሊዬን ሺልንግ ኪሳራ እንደደረሰበትም ታውቋል፡፡

ይሁንና ጉንዜ አሁን ከተደረገው ዳግም መዋቅር በኋላ በሚቀጥለው አመት አየር መንገዱ ከኪሳራ ወጥቶ በሁለት እግሩ እንደሚቆም ተስፋ አድርጓል፡፡

ባለፈው እሮብ እለት የንግድ ልውውጥ መስሪያ ቤቱ የአየር መንገዱን የአክሲዮን ሽያጭ  አክሲዮኑን መግዛት የሚችሉ ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት በሚል ሳቢያ ለ15 ቀናት አራዝሟል፡፡

የፋይናንስ መልሶ ማደራጀቱ ሁሉንም ነባር ባለአክሲዎኖች ያላቸውን ድርሻ በ95 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም አየር መንገዱ ያለፈው ግማሽ የበጀት አመቱ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ባለሃብቶችን ሰብስቦ በሚመጣው አርብ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡