ብአዴን በመማርና በመተራረም ስብዕና መርህ ለበለጠ ውጤት ይተጋል- አቶ ደመቀ መኮነን

 ኤብአዴን በመማርና በመተራረም ስብዕና መርህ ለበለጠ ውጤት እንደሚተጋ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮነን አስታወቁ።

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 37ኛው ዓመት የምስረታ በዓል በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በደማቅ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው። 

በበዓሉ ላይም የብአዴን ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነንን ጨምሮ ነባር የድርጅቱ ታጋዮች እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮነን በበዓሉ መክፈቻ እንደተናገሩት፥ “ብአዴን/ኢህዴን በመማርና በመተራረም ስብዕና መርህ ለበለጠ ውጤት ይተጋል” ብለዋል።

“ሀገራዊና ህዝባዊ ትግላችንን የሚያደናቅፉ አመለካከቶችና ድርጊቶችን ለመዋጋት አባላትና የድርጅት አመራሩ አሁን በተሃድሶ የጀመሩትን ንቅናቄ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል” ነው ያሉት።

ሊቀመንበሩ አያይዘውም፥ ብአዴን የጀመራቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በፍጥነትና በጥራት በሁሉም መስክ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረባረብም ተናግረዋል።

“ወጣቱ ትውልድ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን ሀገራዊ ህዳሴ ሊያጠናክር ይገባል” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በብአዴን 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ እህት እና አጋር ድርጅቶች የእንኳን አደረሳችሁ የአጋርነት መልእክንታቸውን አቅርበዋል፡፡

ኦህዴድን በመወከልም አቶ እሸቱ ደሴ ባደረጉት ንግግር፥ ኢህዴን ከመስረታው በትጥቅ ትግል ጀምሮ እየተጠናከረ የመጣና ለአሁኗ ኢትዮጵያ እውን መሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ድርጅት ነው ብለዋል።

የኦህዴድ እና የብአዴን አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥምል አቶ እሸቱ ተናግረዋል።

ደኢህዴንን በመወከል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያቀረቡት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፥ በኢህአዴግ በተሃድስዎ ንቅናቄ የብአዴን ሚና ትልቅ ነበር አሁንም በዛው እየቀጠለ ያለ ድርጅት ነው በዓሉን ስናከበር በታላቅ ኩራትና ደስታ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሽፈራው አክለውም፥ ኢህዴን/ብአዴን ህበረ-ብሄራዊ ሁኖ ተደራጅቶ ለትግሉ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ድርጅት ነው ብለዋል።

በብአዴን 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ህውሃትን በመወከል የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወልደ ገብረጻድቃን ባስተላለፉት መልእክት፥ "በዓሉን ስናከብር 37 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰን የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ግድ ይለናል” ብለዋል። 

“ኢህዴን በተመሰረበት ጊዜ ተስፋ አስቆራጭና አስቸጋሪ የጨለማ ዘመን ነበር” ያሉት አቶ ተወልደ፥ “ጥቂት የህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ከዴሞክራሲያውያን ኃይሎች ጋር በመሆን ህዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው ያካሄዱት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎና የከፈሉት መስውዋዕትነት ማስታወስ ተገቢ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

አጋር ድርጅትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ኢንጅነር ሀይሻ መሀመድ በበኩላቸው፥ ኢህዴን/ብአዴን ለአጋር ድርጅቶች የሚያደርገው ድግፋ የላቀ መሆኑን ገልፀወዋል።

ኢህዴን/ብአዴን በትግል ሂደት ያመጣውን ውጤቶች መሰረት በማድረግ ክልሎቹ ልማቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አደራሽ በተከበረው በዓል ላይም ለ2 ሒህ 40 የድርጅቱ ታጋዮች እውቅና ተሰጥቷል-ኤፍ ቢ ሲ