በስህተት ለ20 ዓመት የታሰረው አሜሪካዊ 10 ሚሊየን ዶላር ሊከፈለው ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2008(ዋኢማ)- የግድያ ወንጀል ፈፅሟል በሚል ለ20 ዓመታት ዘብጥያ ያሳለፈው ወጣት ከ10 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ሊከፈለው መሆኑ ተሰምቷል።

ፍራንሲስኮ ካሪሎ የተባለው ወጣት የ16 አመት ታዳጊ እያለ ነበር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1991 ዶናልድ ሳርፒ የተባለ ግለሰብ በጥይት ተኩሶ ገድሏል ተብሎ የታሰረው።

ካሪሎ በዚህ በተወነጀለበት ጉዳይ የእድሜ ልክ እስራትም ይፈረድበታል።

በወቅቱ የዓይን እማኝ ነበርኩ ያለ ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍራንሲስኮ ካሪሎ በታጠቀው መሳሪያ ዶናልድ ሳርፒን ገድሎታል በሚል የምስክርነት ቃሉን የሰጠው ግለሰብ በ2011 ይህንኑ ቃሉን አጥፏል።

ምስክሩ “ገዳዩን ማየት አልቻልም ነበር” በማለቱም በስህተት የምስክርነት ቃል ታስሮ የነበረው ካሪሎ ከ20 አመታት በኋላ ከእስር ቤት ወጥቷል።

ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ዳኛም የአይን እማኝ ነኝ ብሎ የቀረበው ምስክር ያቀረበው መረጃ የተሳሳተ እና የተቀነባበረ ነው በማለት ያለምንም ወንጀል ለ20 አመታት በእስር ያሳለፈው ካሪሎ እንዲፈታ እና ካሳ እንዲከፈለው አዟል።

የሎስ አንጀለስ ግዛት (ካውንቲ) ለግለሰቡ 10 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚከፍል መሆኑንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።(ኤፍ. ቢ. ሲ)