ጋና የምርት ገበያ አቋቋመች

ጋና በምዕራብ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የምርት ገበያ ማቋቋሟን አስታወቀች፡፡

ለአመታት ሀገሪቷ የተለያዩ ሸቀጦችን በዘልማድ ትገበያይ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ነጋዴውም ሆነ ገበሬው ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ አድርጎ ቆይቷል፡፡

የንግድ ልውውጡ ህግ እና ስርአት ያልነበረው  በመሆኑ የገበያ ትስስርን ከመፍጠር እና የምርት ብክነትን ለመታደግ አዳጋች ሆኖ የቆየ ከመሆኑም ባለፈ መንግስት ከዘርፉ መጠቀም አለመቻሉም ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ይህ አዲሱ የምርት ገበያ በርካታ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ እንደሚታመን ብሎምበርግ ዘግቧል፡፡

የምርት ገበያው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን  የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን የገበያ ትስስር እንደሚያጠናክርም ይታመናል፡፡

የምርት ገበያው ባሳለፍነው ማክሰኞ በዋና ከተማዋ አክራ በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያውን ግብይትም በእለቱ እንደፈፀመ ታውቋል፡፡

ገበያው በተለይ ዝቅተኛ ምርት ለሚያስገቡ ገበሬዎች የገበያ ትስስር በመፍጠር ለማበረታታት እና የምርት መጠናቸውንም ለማሳደግ የሚያግዝ ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህ ጉዳይ ምርት ገበያው የበለጠ ትኩረት አድርጎ የሚሰራበት  ተግባር እንደሆነ የምርት ገበያው ዋና ዳይሬክተር ካዲ አልፋህ ይገልጻሉ፡፡

ለአመታት የጋናን የግብርና ምርት ለማሳደግ የተለያዩ ሰራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የሚፈለገውን ያክል ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ የገበሬ ማህበራት ሳይቀሩ ግኑኝነታቸው የላላ እንደነበር ተነግሯል፡፡

ግብርናውን ለማዘመን እና ምርትና ምርታማነትንም ለማሳደግ የገበያ ትስስሩን ማሳደግ ሰለሚገባ የምርት ገበያው ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ግብይቱ የሚካሄደው ምርቱንና የምርቱን ባለቤት ማንነት ባስጠበቀ መልኩ እንዲሆን እና ያለ አገናኝ  በቀጥታ መገበያየት ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ የህብረት ሥራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶች የግብይት መድረክ በማዘጋጀት ይከናወኗል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግብይቱን ማካሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦች፣ የህብረት ሥራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶች አስፈላጊ መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ በማድረግ በቀጥታ እንደሚሣተፉ ታውቋል፡፡

የጋና የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እ.አ.ዘ.አ በ2017 አጠቃላይ 6 ነጥብ 1 በመቶ የምርት እድገት ያሳየ ሲሆን በዚህ አመት 2 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ እንደሚያሳይ ተገምቷል፡፡   

ምርት ገበያው በመጀመሪያ አመት ብቻ ከ30 እስከ 50 ሺህ ቶን እንደሚያገበያይ የተገመተ ሲሆን ይህን ልውውጥ ከዚህም በላይ ለማሳደግ እንደሚሰራ የምርት ገበያው ዋና ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡

ጋና በካካዋ ምርት በዓለም ሁለተኛ ስትሆን የምርት ገበያው መጀመር የዚህን ምርት ግብይት ፍታሀዊ ሊያደርገው ይገባል ተብሏል፡፡

የግብይት ስርዓቱ ለቸኮሌት አምራቾች እና ለገበሬዎችም ጥሩ እንድል እንደሆነ ተነግሯል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡