ድራይቭ ቴክ ኩባንያ በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ለመገጣጠም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተስማማ

"ድራይቭ ቴክ" የተሰኘው የኮርያ ኩባንያ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ መኪኖችን መገጣጠም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ ሁኔታ በማጥናት በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ መኪኖችን ለማምረት ወስኗል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ መኪኖችን በማምረት የተሰማራው ‹‹ድራይቭ ቴክ›› የተሰኘው የኮርያ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ምርቶችን በማምረት እና በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን በመገጣጠም ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ነው የተፈራረመው፡፡ 

ስምምነቱን የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከርና የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ዩን ዮንግ ቼይ ተፈራርመዋል፡፡

የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር ስምምነቱ ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን በማፈላለግ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለማምጣትና የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን በዚህ አይነት ዘርፍ ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በቅርቡ በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን የገበያ ጥናት እንዳጠናቀቀ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡