ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላትን ስምምነት ከሩስያ ጋር ተፈራረመች

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በህክምና፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላትን የትግበራ ስምምነት ከሩስያ ጋር ተፈራረመች፡፡

በሩስያ በተካሄደው 11ኛው “አቶምኤክስፖ” ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና የሩስያ ስቴት አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ጀኔራል አሌክሲ ሌካቼቭ ናቸው የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ስምምነቱን የፈረሙት፡፡

የትግበራ ፍኖተ ካርታ ስምምነቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በግብርና፣ የህክምናውን ዘረፍ ለማዘመን፣ ለማምረቻው ዘርፍ ግብዓት እና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በተለይ በአለም እያደገ የመጣውን የህክምና ዘርፍ በኢትዮጵያ ለማዘመንና የቀዶ ጥገና ህክምናን የተቀላጠፈ ለማድረግ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት በዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆነ የኃይል ማመንጫ ኢትዮጵያ መላቀቅ አለባት ያሉት ሚኒስትሩ ፊታችንን ወደ ድብልቅ ኢነርጂ እናዞራለን ብለዋል፡፡

የአቶም ኤክስፖ ለ11ኛ ጊዜ በሩስያ ሲቺ ከተማ ተካሂዷል፡፡ (ምንጭ፡- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)