የፓሪሱ ጥንታዊ የኖተርዳም ካቴድራል ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ

በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሚገኘው ጥንታዊው የኖተርዳም ካቴድራል ህንጻ ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ።

የእሳት አደጋው ምክንያት እስካሁን ባይታወቅም ለህንጻው እየተደረገ ካለው እድሳት ጋር ሳይያያዝ አይቀርም ተብሏል።

የእሳት አደጋ ሰራተኞችም እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።

ባለፈው የፈረንጆች አመት ከህንጻው እርጅና ጋር በተያያዘ አስቸኳይ ጥገና ማድረግ የሚያስችል ገንዘብ እንዲመደብለት ሲጠየቅ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።

እድሜ ጠገቡና የፓሪስ መለያ ከሆኑት ታሪካዊ ህንጻዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የካቴድራል ህንጻ በእርጅና ምክንያት መሰነጣጠቅ ጀምሮ እንደነበር ይነገራል።

በፓሪስ እምብርት የሚገኘው ይህ ካቴድራል ግንባታው በ1345 ዓ.ም የተጠናቀቀ፣ 128 ሜትር ርዝመትና 69 ሜትር ቁመት ያለው የ4ኛው ክፍለ ዘመን አስደናቂው የፈረንሳይን የጎቲክ ሥነ ሕንፃ ምጥቀት የሚንፀባረቅበት የካቶሊክ ካቴድራል ነው።

ይህ ታሪካዊ ካቴድራል ደራሲ ቪክቶር ሂጎ በ1831 ባሳተመው 
The Hunchback of Notre Dame ወይም (Notre-Dame de Paris) በሚለው ልብወለድ መፅሃፉ ዝናው ከናኘ በኋላ በአለማችን ከፍተኛ ጎብኚዎች መሳብ የቻለና በአመት 13 ሚሊዮን ቱሪስቶች የሚመለከቱት አስደናቂ ቦታ ሆኗል።

በፈረንሳይ አብዮት ካቴድራሉ የተጎዳ ቢሆንም፣ ከአብዮቱ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው ናፖሊዮን ቦናፓርቴ ካቴድራሉን ከታደጉት የሃገሪቱ መሪዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው።