አልሸባብና ጭፍን ፖለቲከኞች

ተስፋዬ ለማ

የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ህዝቦች እንደ ሌሎች የአህጉሪቱ ዜጎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ለዘመናት በድህነት አረንቋ ተዘፍቀው ለስደትና ለጉስቁልና ሲዳረጉ ኖረዋል። የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የሰለጠኑ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የተነሳ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን በበቂ ሀኔታ ሳያገኙ በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች ሲታመሱ መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

እ.አ.አ. ከ1990ዎቹ ወዲህ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሠላም፣ መረጋጋትና ልማት በቀጠናው አገራት በጎ ተጽዕኖ እያሳደረ መጣ። ሆኖም ግን ይህንን በጎ የሠላምና የልማት ጉዞ የሚያሰናክሉ የቀጠናውን ሠላም የሚያደፈርሱ እኩይ ተግባራት ሙሉ በሙሉ መገታት አለመቻሉ በቀጠናው ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ ግጭቶች ጦርነቶችና የሽብር ተግባራት መረዳት ይቻላል።

በምሥራቅ አፍሪካ ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አካላት አንዱ አልሸባብ ነው። አልሸባብ ከአልቃይዳ ጋር ቁርኝት ፈጥሮ የኅብረተሰቡን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ለማወክና የቀጠናውን ሠላም ለማደፍረስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እስላማዊ መንግሥትን በመመስረትና የእስልምና ኃይማኖት አክራሪነትን ለማስፋፋት የኃይማኖት ነጻነትን ለማፈን ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ ያለው አልሸባብ ከምድረ ሶማሊያ አልፎ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ በመሳሰሉ አገራት የተለያየ ክብደት ያላቸው የሽብር ተግባራትን በተለያየ ወቅት መፈፀሙ የሚታወቅ ነው።

በሠላማዊ ዜጎች ላይ የሽብር ተግባራትን እየፈፀመ የሚገኘው ጽንፈኛው የአልሸባብ ቡድን በተለይም በሶማሊያ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ አገራት እስላማዊ መንግሥታትን ለማቋቋም ይህንን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ቀጠናውን የሁከትና የሽብር አውድማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ተከትሎ ኢትዮጵያ ችግሩን ቀድማ በመገንዘብ በወሰደችው እርምጃና የአፍሪካ ህብረት አገራትም ባደረጉት የተባበሩት ወታደራዊ ሥምሪት የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ለማተራመስ የያዘው አጀንዳ ሳይሳካለት ከጠንካራ ይዞታው ተፈናቅሎና አባላቱ ተበታትነው በተራ የሽብር ተግባራት ተሰማርቷል።  

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚናገሩት ግን ቡድኑ በቀጠናው ለሚገኙ አገራት ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን ነው። ሶማሊያን መነሻ በማድረግ በቀጠናው የሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን የሚያደናቅፉና የሕዝቦችን  ሠላምና መረጋጋትን የሚያውኩ የተለያየ ክብደት ያላቸው የሽብር ተግባራትን በሰፊው ለመፈፀም ያልተቆጠበ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

ቡድኑ በሶማሊያ ለማቆጥቆጥ ባደረገው ጥረትም ሆነ ባለፉት ዓመታት ለወሰዳቸው በርካታ የሽብር ተግባራት እንደ ብራዘርስ ሁድና አልቃይዳ ከመሳሰሉ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖች የሥልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል።

የአልሸባብ አመራር አባላት በ1990ዎቹ ወደ አፍጋኒስታን በማቅናት በዚያች አገር እስላማዊ ጽንፈኝነትን ለማስፋፋት በነበረው ፍልሚያ ተሳትፈዋል። እስላማዊ መንግሥትን የመመሥረት አጀንዳ አንግበው ከሚፋለሙ ወገኖች ጋር ድንበር ተሻግረው በመሄድ የቻሉትን ያህል ሽብር ለመፍጠር ይጣጣራሉ። ከአልቃይዳ ሙሉ ድጋፍ ይደረግለታል። 

አልቃይዳ በሽብር ተግባር መንቀሳቀስ የጀመረውና የተለያዩ የሽብር ተግባራትን የፈጸመው  ቀደም ብሎ ቢሆንም  የአሜሪካ መንግሥት በሽብር የተፈረጀው ግን እ.ኤ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 በአሜሪካ መንትያ ሕንጻዎች ላይ ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ መሆኑ ይታወቃል። 

ከዚያን ጊዜ በኋላ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሽብር ቡድኑን ለዓለም ኅብረተሰብ  በማስተዋወቃቸውና የሚሰራውን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ በሚል የከፈቱት ዘመቻ የቡድኑን ህልውና የበለጠ ማጠናከር የቻለ እንደነበርም በርካቶች ያምናሉ።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ ክንፎቹን እያጠናከረ በመጣበት ወቅትም በምሥራቅ አፍሪካ መጀመሪያ አልሸባብን ከዚያም ውሎ ሲያድር እነ ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን የመደገፍና የማጠናከር ተግባራትን አከናውኗል።

በአልቃይዳ የሚታገዘው አልሸባብ በሶማሊያ ይዞታውን እያጠናከረ በመምጣት በእስላማዊ  መንግሥት በሸሪአ ሕግ የምትመራ ታላቋን ሶማሊያ ለመመሥረትና የምሥራቅ አፍሪካ አገራትንም ወደ ተመሣሣይ ጎዳና አስገድዶ ለመውሰድ አልሞ መንቀሳቀስን መረጠ።

በዚህ እሳቤ አደረጃጀቱንና የዕለት ተለት እንቅስቃሴውን እየቀቃኘ የመጣው አልሸባብ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረት ከተባለው አክራሪ ድርጅት ጋር በመቀናጀት እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾን መቆጣጠር ቻለ። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ላይ “የጀሃድ” ጦርነትን አወጀ።

በዚህ መልክ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ የጀመረው አልሸባብ በተለይ ሶማሊያን በመቆጣጠር ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማተራመስ ያወጣው እቅድ የኢትዮጵያን ልማታዊ መንግሥት ከልማቱ ሊያደናቅፈው እንደሚችል ምልክት አሳየ፡፡  የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ቡድኑ ወደ አገሪቱ ዘልቆ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት አልሸባብ ወደሚገኝበት የሶማሊያ ክልል በመግባት ከነበረው የሽግግር መንግሥት ጋር በመተባበር የሽብር ቡድኑን መምታት አስፈላጊ መሆኑ እምነት ተያዘ።

በወቅቱ በቀጠናው የነበረውን ሠላም ለማደፍረስ በሚያስችል መልክ ይንቀሳቀስ የነበረው አልሸባብ የሶማሊያ ወጣቶችን እየመለመለ በሽብር ተግባር ለማሰማራት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት በመሆኑ ይዞታውን መምታትና ቡድኑን ማዳከም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር። በዚህ መልክ አልሸባብና የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረትን መምታትና መበተን ካልተቻለ የአፍሪካ ቀንድ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ጅምር ከእንጭጩ መቀጨቱ አይቀሬ  ነበር። ዘላቂ ሠላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ይህንን ፀረ ሠላም የሆነ አሸባሪ ቡድንን መዋጋትና ማዳከም ብቸኛው አማራጭ እንደነበረም የሚካድ አይደለም።

የአልሸባብና የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕሕብረት ዓላማ በቀጠናው ያጎጠጎጠውን ዴሞክራሲ የሚያቀጭጭና የኃይማኖት ነጻነትን የሚገፍ ነበር። የእስልምና መንግሥትና የእስልምና ኃይማኖት ብቻ ለማስፈን ያለመ ትግል ያደርግ ነበር። የሌሎች ኃይማኖቶች ህልውና ይቅርና ከእስልምና ኃይማኖት ውስጥም የሰለፊያ እምነት ብቻ የበላይነት አግኝቶ ሌሎች የእስልምና እምነቶች እንዲደፈቁ የሚፈልግ ነው።

በአልሸባብ፣ በእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረትና በተባባሪ አንዳንድ የአካባቢው መንግሥታት ምክንያት የተደቀነውን አደጋ ማክሸፍ የሚቻለው ቡድኑን በወታደራዊ ኃይል በመምታት እንደሆነም የብዙዎች እምነት ነበር፡፡ በመሆኑም  በወቅቱ ሶማሊያን ያስተዳድር የነበረው የሽግግር መንግሥት ለዓለም ኅብረተሰብ፣ ለአፍሪካ ሕብረትና በተለይ ደግሞ ለጎረቤት አገር ኢትዮጵያ የይድረሱልኝ ጥሪ አቀረበ።

አልሸባብና የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረት በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ አገራት የጦርነት አዋጅ ከማስተጋባት በተጨማሪ በሶማሊያም የከፋ ሁኔታ ፈጥረው ነበር። የሶማሊያዊያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በመግፈፍ የሰለፊያ ኃይማኖት ተከታዮች ያልሆኑ የእስልምና እምነቶች ላይ ዘመቻ ከፍተዋል። ሶማሊያዊያን ህጻናትና ሴቶች ይገረፉ ነበር፤ በርካታ ዜጎችም በሆነው ባልሆነው ይደበደቡ፣ ይሰቃዩና ለእንግልት ይዳረጉ ጀመር። ቡድኑ ሕዝቡን ለሥቃይ በመዳረጉና በዚያች አገር ውጥረትና ችግር በመፍጠሩ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት በህዝቡ ስም ጥሪውን አቅርቧል።

ከዚህ በመነሳት ነው ኢትዮጵያ ሶማሊያን ተቆጣጥሮ የነበረው አክራሪ ኃይል እንዲበተን ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለችው። አንድም በራሷ ላይ የታወጀባትን የጅሃድ ጦርነት ለማክሸፍ በሌላ በኩል ደግሞ በአልሸባብ ጽንፈኛ አገዛዝ ለሥቃይ ተዳርገው የነበሩ የሶማሊያ ህዝቦችን ለመታደግ ሲባል ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል። የሶማሊያን ችግር በዋናነትና በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በዜጎቿ ቢሆንም የነበረው የሽግግር መንግሥትና ህዝቡ በወቅቱ የተደራጀውን የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረትንና አልሸባብን ለመቀልበስ አቅም አልነበረም፤ ይህንን አቅም ለመፍጠር የአልሸባብን አከርካሪ ለመምታት ነበር ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ ለመላክ የተገደደችው።

ህዝቡ የፈለገው አስተዳደር በአገሪቱ እንዲኖር ለማድረግ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ ለመላክ እምነት በያዘችበት ወቅት ጉዳዩን ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደረገ። ያኔ ነበር አንዱ የተቃዋሚዎች ክህደት የተገለጠው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በነበራቸው የሥልጣን ጥም ምክንያት የአገርንና የህዝብን ሉዓላዊነት ሸጠዋል። ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ካወጀ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድን ጋርም ተባብረዋል። የኢትዮጵያን ግስጋሴ ለመግታት ጥረዋል። በአገሪቱ ሁከት እንዲፈጠር ማስነዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ካወጀ ቡድን ጋር በመወገን ከፍተኛ ክርክር ያደርጉ ከነበሩት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር በመተባበር ላይ የሚገኙት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች እንደነበሩ ይታወቃል። እንደ መድረክና አንድነት የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በተጨፈነ አስተሳሰብ ህዝባቸውንና አገራቸውን ክደዋል። ለመደራጀትና የፈለጉትን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ያስቻላቸውን ህገ መንግሥት በኃይልና በሽብር ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል።

የመላው የኢትዮጵያ ህዝብና የዓለም ኀብረተሰብ ድጋፍ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱን ወደ ሶማሊያ በመላክ አልሸባብንና የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረት አከርካሪ በመምታት በኢትዮጵያም ሆነ በሶማሊያ ለመፈፀም የታቀደው እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።

ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ በማስገባት አልሸባብን ለመዋጋት ካነሳሳት ምክንያቶች አንዱ የሶማሊያ ህዝብ እያታረደ፣ እየተገደለና እየተሰቃየ ስለነበር ነው፡፡  በሌላ ጎኑም በሶማሊያ የወቅቱ የሽግግር መንግሥት የኢትዮጵያን ድጋፍ በመጠየቁ እንደሆነና እንደ ጎረቤት አገርና ህዝብ በሥቃይ ላይ ያለውን የሶማሊያን ህዝብ መታደግ አስፈላጊነትን በማመን ጭምር ነበር።

በዋናነት ደግሞ በሶማሊያ ይዞታውን እያጠናከረና ወጣት ሶማሊያዊያንን እየመለመለ በሽብር አስተምህሮ እያሰማራ የሚገኘው የእስልምና ፍርድ ቤት ሕብረትና አልሸባብ  በኢትዮጵያ ላይ “ጂሃድ” ያሉትን ጦርነት በማወጃቸው ነበር።

ያ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሪቱ የነበሩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በጭፍን የሚመሩ፣ አገርንና ህዝብን ከግል ጥቅማቸው ማስቀደም የማይችሉ የሥልጣን ጥመኞች እንደነበሩ ህዝቡ የተረዳበት ወቅት ነው። በድምር ሲታይ ደግሞ በአገሪቱ የነበረው የተቃውሞ ፖለቲካ ጭፍንነትን የሚያጎላ እንደነበር ለመረዳት መንገድ ከፈተ።

መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ ዘልቆ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወሰነውን ውሣኔ ተግባራዊ በማድረጉ በሞቃዲሾ ይዞታውን አጠናክሮ ያቅራራ የነበረው የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረትና አልሸባብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመቶ ተበተነ። የእስላምና ፍርድ ቤቶች ሕብረት አመራሮች የተወሰኑ አባሎቻቸውን ይዘው ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ ተሰደዱ።  የአልሸባብ አመራሮች ደግሞ ከጦርነቱ የተረፉ አባሎቻቸውን ይዘው በደቡብና መካከለኛው የሶማሊያ ክፍል ተበታተኑ።

የተበታተነው አልሸባብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ የሽብር ተግባራቱን አጠናክሮ ቀጠለ። የዘርፉ ተመራማሪዎችና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ በእነዚህ ዓመታት ቡድኑ በደቡብና በመካከለኛው ሶማሊያ ሙሉ የሽምቅ ውጊያና የሽብር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ።

ሮብ ዋይዝ የተባሉ የፀረ ሽብር ኤክስፐርትና ተመራማሪ ’’አልሸባብና የኢትዮጵያ እርምጃ’’ በሚል በሰጡት ትንተና ኢትዮጵያ በሶማሊያ ተንሰራፍቶ በነበረው አክራሪ ኃይል ላይ የተመጣጠነ እርምጃ ከወሰደችና እርምጃውም በአሜሪካ መንግሥትና በአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ በማግኘቱ  አልሸባብ ሊያንሰራራ በማይችልበት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁንና የሶማሊያ አመራሮች እርስ በርስ አለመግባትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም ቡድኑ ከዓለም ሽብርተኞች ቡድን ከአልቃይዳ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላሰለሰ ጥረት በማድረጉ አሁንም ድረስ ሥጋት ሆኖ ዘልቋል።

የአልሸባብ መሪዎች የዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አልቃይዳ እንቅስቃሴና የሽብር ተግባራትን በከፍተኛ ደረጃ ማዳነቅና ማሞካሸትን ሥራዬ አድርገው የያዙት ከዚያ የሽንፈት ማግሥት በኋላ እንደነበርም ተመራማሪው ይናገራሉ። እንደ ኤክስፐርቱ ገለፃ የምዕራብ አገራት በአልቃይዳ ላይ ያደርጉት የነበረውን ዘመቻ ለማጣጣልና ለማውገዝ ቡድኑን የሚቀድም አካል አልነበረም።

አልሸባብ የምሥራቅ አፈሪካ የሽብር እንቅስቃሴ በኦሳማ ቢን ላደን ከሚመራው አልቃይዳ ጋር በቀጥታ የማቆራኘት ተግባራትን በማከናወን ቀጠናውን በሽብር የማናወጥ ተግባሩን አጠናከረ። በአልሸባብና በአልቃይዳ ቀደም ሲል በሥውር የነበረውን ግንኙነት በግላጭ አልሸባብ የአልቃይዳ ታማኝ ክንፍ እንደሆነ አስታወቀ። ከአልቃይዳ አስፈላጊውን ድጋፍ  እያገኙ መንቀሳቀስ ጀመረ። ከአልቃይዳ ባገኘው ድጋፍም እ.አ.አ በ2010 ዓ.ም በኡጋንዳ ካምፓላ የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታን ለመመልከት በተሰበሰቡ ንጹኃን ዜጎች ላይ ቦምብን በማዝነብ የሰባ አራት ዜጎችን ህይወት ቀጠፈ።

ወደ ሶማሊያ ወታደሮቻቸውን ለላኩ አገራት እንደ ኡጋንዳ ዓይነት ዘግናኝ እልቂት ያጋጥማቸዋል ሲልም አስጠነቀቀ። ወታደሮቻቸውን ከሶማሊያ እንዲያስወጡም ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

ኡጋንዳ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ የላከችው እ.አ.አ. በ2007 በአፍሪካ ሕብረት ሥር በወቅቱ የነበረውን የሶማሊያ የሽግግር መንግሥትን ለማገዝ እንደነበር ይታወቃል። በተባበሩት መንግሥታት ለሚመራው የአፍሪካ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ኡጋንዳ ከ6000 የሚበልጡ ወታደሮቿን አሰማርታ ነበር። እንዲሁም ኬንያ 5500፤ ብሩንዲ 5430፤ ጅቡቲ 960 እና ሴራሊዮን 850 ወታደሮችን አሰማርተው እንደነበር ይታወቃል።

የአልሸባብ ኃይማኖታዊ አባት ነኝ ባዩ ሼክ ሐሰን ጣሂር አወይ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ በዚያድባሬ አገዛዝ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ባወጀችበትና ወረራ ባደረገችበት ወቅት ጦርነቱን ከመሩ የዚያድባሬ ኮሎኔሎች መካከል አንዱ ነበር።

የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የሥልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግለት አልሸባብ ይዞታውን በሶማሊያ ለማጠናከርና በየአገራቱ የሚገኙ ቡድኖችን በማደራጀት የሽብር መረቡን ለማስፋት ባደረገው እንቅስቃሴም ግለሰቡ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይነገራል። ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ የሽብር ቡድኖች ናቸው።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እነዚህን ቡድኖች ከአልሸባብ ጋር በማቀናጀት አሸባሪ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ዳሩ ግን በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁኔታ በእውነት ግራ የተጋባ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ። ሽብርተኝነትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲደግፉ ይታያሉና።

አገሪቱ በአልሸባብ ላይ ዘመቻ በከፈተች ወቅት ያሰሙትን ተቃውሞ ቀጥለውበታል። ኢትዮጵያ እጆቿን ለአሸባሪዎችና ለጽንፈኞች መስጠትና መንግሥትም አገር ሲታመስና ህዝብ ሲታወክ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ይመክራሉ።

እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የፀረ ሽብር ሕጉ ተግባራዊ እንዳይሆንም ያላሰለሰ ጥረትና ተቃውሞ ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህ ከምን የመነጨ ነው? ይህ የሚመነጨው ከውስጥ ማንነታቸው እንደሆነ እሙን ነው። አልሸባብና አንዳንድ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸው አይደል?