የንግድ አሠራር ሥርዓቱን ለማሻሻል ሥልጠና እየተሠጠ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥር 6/2006 (ዋኢማ) – በአገሪቱ አሁን ያለውን የተንዛዛና ኋላቀር የንግድ አሠራር ቀልጣፋ ፤ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ ለአስፈጻሚዎችና አመራሮች ሥልጠና እየሠጠ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሮክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አረጋ ለዋልታ እንደገለጹት ስልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የንግድ ቢሮ አስፈጻሚ አካላትና አመራሮች ነው።

ዘመናዊና ተወዳዳሪ   የሆነ  የንግድ ሥርዓት  በመገንባት  ህዳሴያችንን እናፋጥናለን  በሚል  መሪ  ቃል ከታህሳስ 20 ጀምሮ ለ7 ቀናት በተሠጠው ስልጠና እስካሁን  በአፋር ፤ በኦሮሚያና ጋምቤላ  ብሔራዊ ክልሎች  የሚገኙ 712  ሠልጣኞች ተካፍለዋል።

ከጥር 2 ጀምሮ በሱማሌ ፤ ድሬዳዋ ፤ ሐረሪ ፤ ደቡብና ትግራይ ብሔራዊ ክልሎች የተውጣጡ 451 ሠልጣኞችም በአሁኑ ወቅት ሥልጠናውን እየተከታተሉ መሆኑን አቶ ሽመልስ አያይዘው ገልጸዋል ።  

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሠጠ ያለው ሥልጠና በንግድ አሠራርና ውድድር ማጠናከሪያ ፤ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ፤ በንግድ  ሥራ ፈቃድ ደንቦችና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  እንዲሁም የሸማቾች ጥበቃ በሚሉ በአምስት ርዕሶች ላይ ያተኮሩ መሆቸውን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል ።