ኢትዮጵያ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳላት ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2006/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳላት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬት በአግባቡና በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ የመስኖ ልማት ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛል።

የመስኖ ልማቱ ከ1984 ዓ.ም በፊት ብዙም ትኩረት ያልተሰጠውና የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ ያልነበረው በመሆኑ ከ61 ሺ ሄክታር በላይ የመስኖ ልማት እንዳልነበረ አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ብዙነህ ገለፃ ከ1984 ዓ.ም በኋላ ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የመስኖ ልማት የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ መቀረፁን አስታውሰው፤ በዚህም በመንግስት ከሚለማው ባሻገር በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።

መንግስት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ የመካከለኛና ሰፋፊ መስኖ እርሻ ሽፋንን በ2002 ዓ.ም መጨረሻ ከነበረበት 2 ነጥብ 4 በመቶ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ወደ 15  ነጥብ 4 በመቶ ለማድረስ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል በማለት ገልፀዋል።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ በመካከለኛና ሰፋፊ የመስኖ ልማት በጥናትና ዲዛይን ግንባታ፣ በመልሶ ማቋቋምና ማስፋፋት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አቶ ብዙነህ ገልፀው፤ በእቅድ ዘመኑ በጥናትና ዲዛይን 746 ሺ 334 ሄክታር መሬት የጥናትና ዲዛይን ስራ ለማከናወን የታቀደ ሲሆን፤ በግንባታ ደግሞ 658 ሺ 340 ሄክታር ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም ባለፉት ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 559 ሺ 484 ሄክታር የጥናትና ዲዛይን ስራ ለማካሄድ ታቅዶ 540 ሺ 520 ሄክታር ሲከናወን በግንባታው ደግሞ 453 ሺ 015 ሄክታር ታቅዶ 170 ሺ 913 ሄክታር የመስኖ ግንባታ ተከናውኗል ብለዋል።

በአጠቃላይ እስከ 2004/2005 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 298 ሺ 155 ሄክታር መሬት በመካከለኛና ሰፋፊ የመስኖ ልማት ማልማት ተችሏል በማለት ገልፀዋል።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ 15 የመስኖ ልማት ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ፕሮጀክቶች እየካሄዱ መሆኑን ጠቁመው፤ ከነዚህ መካከል ዘጠኙ በተያዘው የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ አራቱ በ2007፣ አንድ በ2008ና አንድ በ2009 የበጀት ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።