የአሉባልታ ጋጋታ ከእውነታው ሲጣረስ

ሀገሬ በፍርዱ
ፍቅራቸው ደርቶ ብን ብለው ያብዳሉ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል  ብዙ አይዘልቁበትም፤ ወረቱ ያልቅና  እሣትና ጭድ ለመሆን ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡ አንዱ ሌላውን ሊጠልፍ ጀምበር በቂው ነው፡፡ እምነት የሚባል ነገር በመሃላቸው አልፈጠረባቸውም፡፡ እርስ በርስ አይተማመኑም፡፡ ከአንገት በላይ ጊዜያዊ ፍቅር ተሟሙቀው ወዳጅ መስለው ይታያሉ፡፡ ገላልጠው ሲያዩዋቸው እሣትና ጭድ ናቸው፡፡ ለመጠፋፋት ውስጥ ውስጡን ሴራ ይገማመዳሉ፡፡ ሆድና ጀርባ ቆመው ሣንጃ ለመሞሻለቅ፣ ጩቤ ለመማዘዝ አይተዛዘኑም፡፡ ዛሬ ህብረት፣ ነገ ቅንጅት፣ ከነገ በስቲያ ውህደት ለመፍጠር ማን ቀድሟቸው፡፡ አዎ እነሱ እንዲያ ናቸው— እነ መድረክ፡፡
ለመሆኑ መድረክ ማነው? እርግጥ ነው እሣትና ጭድ በሆኑ ፓርቲዎች ጥምረት የሚመራ ስብስብ ነው፡፡ እርስ በእርሱ የማይተማመን ስብስብ፡፡ መለያቸው ሁሌም ማናቸውንም ሀገራዊ ችግሮች በመንግሥት ወይም በገዥው ፓርቲ ላይ ያላላከከበትን አሊያም ሊያላክክ ያልሞከረበትን ጊዜ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ የሁልጊዜ ምኞቱ አሉባልታ ወሬዎችን ቋጥሮና መሠረተ ቢስ ዱስኩሮችን ለቃቅሞ እንዲህ ሆነ እንዲህ ተባለ እያሉ ማራገብና ማጯጯህ ተዘውታሪ ተግባሩ እየሆነ መጥቷል፡፡
ማናቸውንም አሉባልታዊ ትርክቶችን በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ላይ መለጠፍ፣ በዚህም በአቋራጭ ሥልጣን ለመቆናጠጥ መቋመጥ የማይጨበጥ ባዶ ተስፋው ነው፡፡ መድረክ ወደ ግንባርነት መቀየሩን ባበሰረበት ማግሥት ብቻ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው  ምናልባትም ስለ ምክንያቱ ሲጠየቅ በመንግሥት ላይ ጣቱን ሳይቀስር የቀረው፡፡ 
ይህም ቢሆን ማጣፊያው አጥሮት እንጂ ብዙ ማለት በተቻለው፡፡ ‘ግንባር እንድሆን የወሰነው መንግሥት ነው’ ለማለት ስላላመቸው እንጂ ይህን ከማለት አይቦዝንም ነበር፡፡ ለምን ባይ ጠያቂ ቢመጣ የማይተማመኑ ባልንጀሮች ስብስብ የሆነው ይህ የተቃውሞ ጎራ መንግሥትን ወይም ገዥውን ፓርቲ የሚያጥላላ እስከሆነ ድረስ ማናቸውንም ፈጠራዎች  እየፈበረከ ከማላዘን ወደ ኋላ አይልም፡፡

የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ነኝ ይላል መድረክ፡፡ እጅህ ከምን ቢሉት ይህ ነው የሚባል የማያሻማና በግልፅ የሚታወቅ፤ ህዝብን በዙሪያው ሊያሰባስብ የሚችል የጠራ የፖለቲካ አማራጭ የለውም፡፡
መድረክ ላይ ላዩ ሲታይ የሊበራሊዝም አቀንቃኝ ይመስላል፡፡ ይሁንና እውተኛ ማንነቱ ሲፈተሽ፤ ፓርቲው እመራበታለሁ የሚለው ከዚህም ከዚያም በተቃረሙ ሃሳቦች መሆኑን ለመገንዘብ ነቢይ መሆን አያሻም፡፡ እነዚህ ቅንጭበጫቢ ሃሳቦችም ወጥ ያልሆኑ፤ ያልተብራሩ፤ ያልተተነተኑና ያልተዘረዘሩ ናቸው፡፡ ለማደናገር ካልሆነ በቀር ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚባለውም ጉዳይ ሲያልፍ አይነካካቸውም፡፡ 
እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ በተከታታይ ፖለቲካዊ ቅስቀሳና ትምህርት ህዝብን ማሳመን የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡ ይህ ተግባር በስብስቦቹ ዘንድ እንደ ነውር፣ እንደ ጠያፍ  ነገር የሚታይ ነው፡፡ ሁሌም ሰበብ አያጡም እንዲህ ሆንኩ፤ እንዲህ ተበደልኩ የሁሌም ጩኸታቸው ነው፡፡ የቤት ሥራቸውን በቅጡ መወጣት ሲሳናቸው ምህዳሩ ጠቧል፤ አፈናና ወከባው ብሶበታል፤ አባልና ደጋፊዎቼ ተሳደውብኛል ዘወትር የሚያላዝኑት እሮሮ ነው፡፡ 
ውኃ የማይቋጥር ሰበባ ሰበባቸውን ትተው ወደ ህዝቡ የሚዘልቁበትን የተግባር እንቅስቃሴ ቢከውኑ መልካም በሆነ ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ መሬት ላይ ጠብ የሚል ያከናወኑት ተግባር ስለሌላቸው ሁሌም ሰበብ መደርደር ነው — ቁልፉ ተግባራቸው፡፡
ለስብስቦቹ ከትናንት መማር ማለት አይታሰብም፡፡ ዛሬም ከትንናቱ መቆሚያቸው  አናጣቸውም፡፡ ትናንት በነበሩበት ቦታ ላይ ሆነው ዛሬም ድረስ የነተበ ቡሉኳቸውን ደርበውና ጊዜ ያለፈባቸውን ድርሳናታቸውን አቧራ ሳያራግፉ መግለጥና ማነብነብን እንደ ትክክለኛ የፖለቲካ ስልት የሚከተሉ አስገራሚ ፍጡሮች ናቸው፡፡ ዛሬም እዚያው ሥፍራ ላይ ሆነው እንዳላዘኑ አሉ፡፡
ስብስቦቹ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ የመንግሥት ሥልጣንን በቀለም አብዮት በሚመራ የጎዳና ላይ ነውጥ በአቋራጭ የመቆናጠጥ ህልማቸው አሁንም ድረስ የሚሰራ ይመስላቸዋል፡፡ መድረክ ትናንት ከህገ – መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጋር በፈጠረው እሰጥ አገባ በምርጫ 2002 በህዝቡ ካርድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ሽንፈት መከናነቡን ዘንግቶታል፡፡

ከትናንቱ ሂደት ሳይማር ዛሬም ባለበት ቆሞ እየዳከረ ነው፡፡ ፀረ ህገ መንግሥታዊ ስልት ቦታ ላይ ሆኖ የአሉባልታ ድቤ እየደለቀ፤ የጥላቻ ዘመቻውን እያጧጧፈ ይገኛል፡፡ የሰሞነኛው እሪታና መግለጫ መቋጫውም የተለየ እውነታን አልያዘም፡፡
በነገር ተንኳሽነታቸው ተለይተው በሚታወቁትና በትናንቱ መኢሶን አፍቃሪ በዛሬው በግንባሩ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና የተነገረን ሰሞነኛ መግለጫ ብዙም አዲስ ጠባይ የለውም፡፡ ያው የተለመደው ዓይነት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ “ኢህአዴግ ‘አንድ ለአምስት’ በሚባል አደረጃጀት ዜጎችን በማደራጀት ህብረተሰቡን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው፣ ሠላማዊ ሰልፍ እንዳንወጣ ታፍነናል እንዲሁም ኢህአዴግ በኃይል እያስገደደ ዜጎችን አባል ያደርጋል። እናም ሌላ ሌላ ብዙ አውርተዋል፡፡ ብዙ አስገራሚ ጥቃቅን ድርሳናትን አነብንበዋል፡፡
ውድ አንባቢያን ይህን ጊዜ አንድ ጥያቄ በአዕምሮዎ ቢጭርብዎ አይፈረድም፡፡  ‘ለመሆኑ እውን እነዚህ የመድረክ ድርሳናት ውኃ የሚቋጥሩ ናቸውን?፣ በአሁኑ ወቅትስ እነዚህን ጉዳዩች ማንሳት ለምን አስፈለገ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ መድረኮች ‘ወደ ሥልጣን እርካብ ያወጣጣናል ብለው ካመኑ ምንም ሆነ ምን መለጣጠፍ መለያ ታክቲካቸው ነው፡፡ ወደ ሥልጣን ያቀርበኛል ብለው ከገመቱ  ማንኛውንም ነገር በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ላይ ከመለጠፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው፡፡ ለማንኛውም የመድረክ ሰዎች በመግለጫ መልክ የደሰኮሩትን በጥቂቱ እንፈታትሻቸው፡፡
መድረክ በመግለጫው የገዥው ፓርቲ የ‘አንድ ለአምስት’ አደረጃጀት አሠራር ሀገሪቱ ለጀመረችው የብልጽግናና የልማት እቅድ ሲባል የተዘጋጀ እንጂ፤ ስብስቡ “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንዲሉት ዓይነት ስልጣንን ስለሚያልም ብቻ እርሱ እንዳለው ለፖለቲካ ቅስቀሳ ተግባር ሲባል የተፈጠረ አይደለም። ማንኛውም ጤናማ ዜጋ ልብ እንደሚለው  በየትኛውም የሥራ መስክ ያልተደራጀ የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት መስክ ስኬትን ሊያስመዘግብ እንደሚያዳግተው ነው፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ በመንግሥትና በህዝቡ የተያዘውና ውጤት እየተገኘበት ያለው ታላቅ ተግባር በድህነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ ነው። ታዲያ ይህ ዜጎች አንገታቸውን ደፍተው እንዲሄዱ ያደረጋቸውን ድህነት ለመቅረፍ ብሎም ለማስወገድ ሁሉም ዜጋ፣ በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው አርሶ አደር ተደራጅቶ ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት ግዴታው ይሆናል፡፡
ማንኛውም ዜጋ በየተሰማራበት ልማታዊ ክንዋኔ በምን ዓይነት ሁኔታ በምጣኔ ሃብቱ ላይ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ለመጫወት መደራጀቱ ምን የሚያስከፋ ነገር ይኖረው ይሆን? ይህን ተግባር በመከወን የመሪነት ሚናቸውን የመጫወት ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ደግሞ መንግሥትና ዜጋውን በመምራት ላይ የሚገኘው ገዥው ፓርቲ መሆኑ ችግሩ ምን ይሆን? እናም ሁሉንም ነገር ከሥልጣን ጥመኝነት አንፃር ብቻ እየመዘኑ ጣትን በሌሎች ላይ መቀሰር ምን ይሉት አባዜ ነው?
ለመሆኑ ዜጎችን ለልማት ማደራጀቱ ክፋቱ ምን ይሆን? ሌላው ቀርቶ ፈሩን ስቶ አራምባና ቆቦ እየረገጠ አስቸገራቸው እንጂ፤ በመድረክ ውስጥ በጥርጣሬና በጎሪጥ የሚተያዩትና ለይስሙላ የተጣመሩት ፓርቲዎችም ይሁኑ ‘እናት ፓርቲያቸው’ የተደራጁት አንዳች ውጤት ለማምጣት አይደለምን?…አዎ! የመደራጀት ሃሳቡ እንዲያ ነበር። እርግጥ ነው መድረክ የልማት ሃሳቦችን ለምን እንደሚያጥላላ አይጠፋንም፡፡
እንዲያውም መድረክ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱ ልማት ደንቃራ እንጂ ደጋፊ ሆኖ ሲሆን አላየሁትም፡፡ አብነቶችን እንጠቃቅስ፡፡
እርግጥ ነው፡፡ በየጊዜው የማደናገር ስልቶችን የሚከተሉት እነ መድረክ፤ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የማምታቻ ሃሳብ ይዘው ብቅ ማለታቸውን አንድ በሉ፡፡
መድረክን እንመራዋለን የሚሉት ጎምቱ ፖለቲከኞች ከእንቅልፋቸው በባነኑ ቁጥር ድንገት እየተነሱ ‘ዕቅዱ የማይሳካ ነው፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በመንግሥት የተያዘ ትልም ነው’ በሚል ህዝቡን ከልማት ርብርቡ ሊያዘናጉት ያልሞከሩበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን አንዳችም ውጤት አላገኙም።
እናም ህዝቡ “ዕቅዱ የነገ ማንነቴን አሻግሬ የምመለከትበት እንዲሁም ከተመፅዋችነት የምላቀቅበት ስለሆነ ወግዱ እናንተ አደናቃፊዎች” የሚል ምላሽ በመስጠቱ፤ ፀረ – ልማት የሆኑት ወገኖች ዕጢያቸው ዱብ ብሏል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታን በተመለከተም ህዝቡ ይህን የህዳሴውን ፈር ቀዳጅ ተግባር እውን እንደሚያደርገው ስለተማመነ፤ የእነ መድረክን ፀረ ልማት የከበሮ ድለቃ ሊሰማ አልፈለገም፡፡ ጆሮውንም አላዋሳቸውም፡፡ ይባስ እረፉት፤ እርማችሁንም አውጡ ብሎ ለግንባታው በገንዘቡ፣ በጎልበቱና በእውቀቱ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር፤ የቦንድ ግዥውን አጧጡፏል፡፡ በዚህም ቆሽታቸው አሯል፤ ግብፅ ውስጥ እንዳሉት “የሙባረክ መንፈስ” አራማጆች ሁሉ፣ የሀገሬ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችም ወሽመጣቸው ተቆርጧል፤ እጢያቸው ዱብ ብሏል፡፡     
ሌላ ማሳያ ልጨምር፡፡ ለአቅመ ተቃዋሚነት ያልደረሰው መድረክ በአንድ ወቅትም የሀገሪቱን ልማት በሪፖርት ጋጋታ የሚደናቀፍ ለሚመስለው ሂዮማን ራይትስ ዎች ለተሰኘ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ተቋም የሀገር ውስጥ የቀለም አብዮት ክንፍ ሆኖ በእማኝነት መቅረቡን እናስታውስ፡፡ “የኢትዮጵያ መንግሥት የዕርዳታ እህልን ለፖለቲካ ፍጆታ ይጠቀማል” የሚል አሉባልታን ሲያጯጯሁ ከረሙ፡፡ 
እውነታው ጠፍቷው አይደለም፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉትና እውነታውን ጭምር በመስክ ጉዞ ምልከታ ሳይቀር ባረጋገጡት የልማት አጋር ሀገራት ቡድን (ዳግ) በኩል  የተባለው ሀሰት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ተሰጠ፡፡ ድርጊቱም እንዳልተፈፀመ ተረጋገጠ፡፡ የአሉባልታው አቀንቃኝና ተዋናይ “የገደል ማሚቶ” የነበረው መድረክ በኢትዮጵያ ህዝቦች ፊት የሃፍረት ሸማን ለበሰ፡፡ በእፍረት ሟሸሸ፡፡
ያም ሆነ ይህ መድረክ “ኢህአዴግ ‘አንድ ለአምስት’ እያደራጀ ህብረተሰቡን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው” በማለት በመግለጫነት ያቀረበው መሠረተ ቢስ ሃሳብ የፍራቻው መነሻዎች ሁለት ጉዳዮች ናቸው። አንድም በደፈና ተቃውሞ የሚመራው ስብስብ ‘ህብረተሰብን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር’ ስለሚለው አባባሉ የግንዛቤ እጥረት ያለበት መሆኑነው፡፡ ሌላው ‘አንድ ለአምስት’ የተሰኘው አደረጃጀት መድረክ በአቋራጭ ሥልጣን ለማግኘት ሌትም ቀንም ለሚመኘው የቀለም አብዮት ምቹ አለመሆኑ ነው።
እርግጥ በየትኛውም ነባራዊ ዓለም ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ተቆጣጥሮ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ማስያዝ አይቻልም። ልዩነት ዓለም የሚመራበት ኑባሬ ነው። ልዩነት ተፈጥሮአዊ ውበት ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሊመጣ የሚችለው የጋራ አስተሳሰብ ነው — ልክ እንደ ብሔራዊ መግባባት ዓይነት ማለት ነው። ዜጎች በሁሉም ሳይሆን በአብዛኛው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ሊይዙ ይችላሉ። ለዚህም በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩትን እንደ ህዳሴው ግድብ ዓይነት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በምሣሌነት ማንሳት ይቻላል። ለነገሩ የመድረክ ሰዎች ይህ ሁኔታ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ 
ዋና ዓላማቸው ያገኙትን ነገር ሁሉ በመለፈፍ ተራ የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኙ ስለሚመስላቸው እንዲህ ዓይነቱን እውነታ ሊጋፈጡት አይፈቅዱም፡፡
እርግጥ ከመድረክ ድርጅታዊ ባህሪ ስንነሳ የ‘አንድ ለአምስት’ አደረጃጀትን መፍራቱ አይፈረድበትም። ለምን ቢሉ እንዲህ ዓይነቱ የህዝብ ልማታዊ አደረጃጀት በየደረጃው ተጠቃሚነትን ስለሚፈጥር፣ ለቀለም አብዮት ዓላሚዎች ምንም ዓይነት ክፍተት ስለማይፈጥር ነው። ምንም እንኳን አደረጃጀቱ ከልማት ጋር የተሳሰረ ቢሆንም፤ የእነ መድረክን የቀለም አብዮትን ፍላጎት በማጨናገፍም ረገድ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ሊታወቅ ይገባል፡፡ 
በግልጽ እንደሚታወቀው የቀለም አብዮት በአንድ ሀገር ውስጥ በምርጫ ዋዜማና አመቺ ሲሆንም “የቀለም አብዮተኞቹ” ባለሙት ጊዜ በአንድ ወቅት ሊከናወን ይችላል። ታዲያ ለዚህ ተግባር ክዋኔ በዚያች ሀገር ውስጥ ህዝቡን በተለይም ወጣቱን ክፍል በማደናገር ሊያነሳሳ የሚችል ጠንካራ ተላላኪ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊኖር ይገባል — ዓለም አቀፉ “የቀለም አብዮት ጠበብቶች” እንደሚሉት።
ታዲያ ይህን እውነታ ወደ እኛ ሀገር ስንመለሰው የ‘አንድ ለአምስት’ ልማታዊ አደረጃጀት ህዝቡ በየደረጃው ልማታዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ እያደረገው ነው። ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኝ ህዝብ ደግሞ፣ መድረክ ውስጥ እንደ ተሰገሰጉት “የፖለቲከኛ ቁማርተኞች” የቀለም አብዮት ናፋቂዎችን አሉባልታና ውዥንብር የሚሰማበት ጆሮ የለውም።
የዚህ እውነታ ምክንያቶች ሁለት ናቸው። ቀዳሚው መላው ህዝብ በልማታዊ መንግሥቱ ትክክለኛ ልማታዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ የተጠቃሚነት ደረጃውን እያሳደገ መምጣቱ ነው፡፡ ‘የጎዳና ላይ ነውጥ እናድርግ’ ብሎ የሚያሟርትን የተቃውሞ ጎራ ሃሳብ የሚቀበልበት ምንም ምክንያት ስለሌለው ነው። ሌላው የህዝቡ ንቃተ ህሊናዊ አስተሳሰብ ከተቃዋሚ ተብዬዎቹ የትየለሌ የላቀ መሆኑ ነው።
እርግጥም ህዝቡ ከመድረክ የተሻለ ሁሉን አቀፍ ግንዛቤና ንቃተ-ህሊና ያለው መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች አስመስክሯል። በተለይም ወጣቱ መድረክ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲዘልፈው ጭምር ራሱን በልማታዊ ሥራ ባተሌ በማድረግ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ አልፎታል።
ጨርሶውኑ በመተካካት መርህ የማያምነውና ይህም ያልፈጠረበት በአሁኑ ወቅትም ከፖለቲካ ፓርቲነት ወደ “አዛውንቶች ክበብነት” ተሸጋገሯል የሚባለው መድረክ ያን ሰሞን  የወረፈኝነትን ቦታውን ተረክበው በነበሩት የኦፌዴኑ ሰው ዶክተር ሞጋ ፉሪሳ አንደበት ውስጥ አድሮ ወጣቱን “በብልጭልጭ ነገር ይታለላል” በማለት በስብሰባው ላይ በንቀት እንደዘለፈው አስታውሳለሁ።
የሀገሪቱን ወጣት በልማት ሥራ የተጠመደ፣ አመዛዛኝ፣ ነገሮችን በእርጋታ የሚቃኝ፣ ጉዳትና ጥቅሙን የሚለይ እንዲሁም የጠራ ብሩህ አዕምሮ ባለቤት እንጂ የመድረክ የቁማር ፖለቲከኞቹ እንደሚሉት በብልጭልጭ ነገር የሚታለል አይደለም፡፡
ወጣቱ ዛሬ በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በተለያዩ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ታቅፎ በልማት ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ከድህነት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ የነገ ማንነቱን ብሩህ ለማድረግም ከጊዜ ጋር ሩጫ ላይ ነው፡፡
የሀገሪቱ ወጣት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተኮትኩቶ የበቀለና የዴሞክራሲን ምንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ አመዛዛኝ እንዲሁም ነገሮችን በጥሞና እና በሰከነ አዕምሮ የሚመለከት ከመሆን ባለፈ፤ የሥርዓቱ የነገ ተረካቢ በመሆኑም የሚበጀውንና የሚጠቅመውን መለየት የሚችል ኃይል ነው፡፡
ወጣቱ ደጋፊ ወይም አባል መሆን ከፈለገ ምን ዓይነት የፓለቲካ  ሂደት ውስጥ መግባት እንዳለበት ነጋሪ አያሻውም፡፡ ወጣቱ ክፍል በዕድሜ ለጋ ቢሆንም፤ የሊበራሊዝም አቀንቃኝ መስሎ ለመታየት ከሚጥረውና የሚያብለጨልጭ ነገር ሁሉ ወርቅ እየመሰለው በፈረንጆች የሚዘወር ዴሞክራሲ ከሚያማልለው “ተቃዋሚ ነኝ” ባዩ መድረክ፤ ስለ ዴሞክራሲያዊ አሠራሮችና እምነቶች የተሻለ ግንዛቤ ያለው መሆኑን በተግባር ያሳየ ኃይል ነው፡፡
እናም በአስተዋይነቱ ‘ነገ በአቋራጭ ሥልጣን ብይዝ እመራሃለው’ ከሚለው መድረክ እጅግ የተሻለ በመሆኑ፣ መቼም ቢሆን የእርሱን አሉባልታ ሊሰማው ጆሮውን አያውስም፡፡ ይህ ሁኔታም ለቀለም አብዮት ተላላኪው መድረክ ራስ ምታት ቢሆንበት አይሳቅበትም፡፡ የመድረክ ማንነት በአጠቃላይ ህዝቡ፣ በተለይም በወጣቱ ዘንድ በግልጽ የሚታወቅ ነው መጠላለፉ፤ መፈረካከሱ፤ መነታረኩ፤ መጠላለዙ፤ መቦጫጨቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡
በብሶት አራጋቢ ፖለቲከኝነት የሚመራው መድረክ ስለሚያራግባቸው የአሉባልታ ወሬው ጥቂት ልበል፡፡ “ሠላማዊ ሰልፍ እንዳንወጣ ታፍነናል” ስለሚለው። እርግጥ ይህ ጉዳይ ከቀልድነት የሚያልፍ እንዳልሆነ ማንም አንባቢ አይጠፋውም፡፡ ያለምክንያት አይደለም፡፡
ሁሉም ይቅርና ‘ሰማያዊ’ የተሰኘውና በአንድ በኩል “ሰማያዊ” በሚለው ሥያሜው እየተመራ ምድራዊ ፖለቲከኝነቱን በመተው አክራሪ ኃይማኖተኞችን የሚደግፈው፣ በሌላ በኩልም “ሰማያዊ” ቀለሙን በመጠቀም የቀለም አብዮተኞች ባለሟል ለመሆን የሚሻው ፓርቲ ስንቴ ሠላማዊ ሰልፍ እንደወጣ መቁጠሩ ብቻ በቂ ነው፡፡ መድረክን እንዳሻው የሚያጦዘው አንድነት ፓርቲም እንዲሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን አደባባይ ለሠላማዊ ሰልፍ ምን ያህል ጊዜ እንደወጣ ማስላት ይቀላል ።
ታዲያ እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ፓርቲ ያለው መብት ሌላውም የሚኖረው መሆኑ እየታወቀ እነ “ቁማርተኛ ፖለቲከኞቹ” ለፌዝ ብለው ያቀረቡት ካልሆነ በስተቀር፤ እውነታው ቢመዘን አንድ ጠብታ ውኃ እንደማይወጣው ያስማማናል፡፡ እውነታው ይህ ነው፡፡
የመድረክ “ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላደርግ ታፈንኩ” ብሶት ሽፋን ወዲህ ነው፡፡ ይኸውም መድረክ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ሲያበቃ፣ በየአደባባዩ የሚወጣለት ህዝብ እዚህ ግባ አለመባሉ ሲያሳስበው ማምለጫው ዘዴ ታፈንኩ ማለት ብቻ መሆኑ ነው። እርግጥ ውሸት አራጋቢው መድረክ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን አድርጓል። ይሁንና አሰላለፉ እንኳንስ ለሀገር አስተዳዳሪነት ቀርቶ “ለመንደር አለቃነት” የማይመጥነው መሆኑን ካለፉት ሂደቶቹ ጠንቅቆ የተረዳው ይመስላል፡፡ 
በመድረክ ካባ ስር የተጠለሉት በመንፈስም ሆነ በሥጋ የተለያዩ ፓርቲዎች በለስ ቢቀናቸው ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመናድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሥልጣንን በህዝብ የምርጫ ካርድ ሳይሆን በግርግር ሊጨብጡ የሚሹ፣ በተለያዩ ጊዜያት አመፅ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከሰት ተግተው የሚፀልዩ፣ የሀገሪቱን የልማት ትልም የሀሊት ለመዘወር የሚተጉ ቢይዝላቸው ከሀገሪቱ ደመኛ ጠላቶች ጋር አብረው መስራት የሚፈልጉና ለመሆናቸው የየእለት ተግባራቸው ምስክር ነው፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ የመድረክ ዕጣ ፈንታ ሠላማዊ ሰልፍ በጠራባቸው ከተማዎች ሁሉ ከራሱ ጋር ተሰብስቦ፣ የራሱን ቃርሚያ ወሬዎች ለራሱ አነብንቦ በባዶ ሜዳ ላይ መመለስ መሆኑ የቱን ያህል እንደሚያሳፍር ነው። ራሱ በፈበረከው ማንነታዊ ባህሪ የህዝብ ድጋፍ ሲያጣ “ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላደርግ ታፈንኩ” እያለ መወትወቱ ትዝብት ላይ ከመጣል አልፎ የሚፈይደው አንዳች ቁም ነገር የለም፡፡
ሌላው የመድረክ አሉባልታ “ኢህአዴግ ዜጎችን እያስገደደ አባል ያደርጋል” የሚል ነው። ምንም እንኳን ይህ መግለጫ ዘወትር ምርጫ በተቃረበ ቁጥር የሚለቀቅ ነጠላ ዜማው የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ የስብስቡ አባላት የሚለቁት ይህ ዜማ በማስረጃ ያልተደገፈ፤ የተሰላቸ አሉባልታ ከመሆን አይዘልም።
መድረክ የትኛው ዜጋ መቼ፣ የትና እንዴት ተገድዶ አባል እንዲሆን እንደተደረገ ተጨባጭ ማስረጃ አያቀርብም፡፡ ከዚህ በተረፈ ከባዶ ነገር ተነስቶ እንዲህ ሆነ፤ እንዲህ ተፈጠረ እያሉ በአውላላ ሜዳ መጮህ ትርፉ ምን ይሀን?
ኢህአዴግ በሽኩቻ በሚጠላለፉት የመድረክ ስብስቦች ውስጥ ያሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች እንደሚያራግቡት አሉባልታ ሳይሆን በርካታ የህዝብ ልጆች መስዕዋት ሆነው ያስገኙት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጠናከርና ስር እንዲሰድ ዛሬም ትግሉን አቀጣጥሎ እንደሚጓዝ ነው፡፡ እነሱ ያውሩ፤ የሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ጉዞው ግን ቀጥሏል፡፡