የገጠር ልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ወቅታዊ አፈጻጸም ስኬታማ መሆኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2006 (ዋኢማ) – በገጠር ልማትና በመልካም አስተዳደር ያለው ወቅታዊ አፈጻጸም ስኬታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥቅምት 09 እና 10 ቀን 2006ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በመስኖ ልማት፣ በገጠር የስራ ዕድል ፈጠራ፣ በተቀጀ የተፋሰስ ልማትና  በበልግ ዝግጅት  እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም ሆነ  በመልካም አስተዳደር የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን በግምገማ አረጋግጧል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀ በበጀት አመቱ ካለፉት አመታት በተሻለ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የመስኖ ልማት ስራ እየተከናወነ ነው።

ሁሉንም ዓይነት የውሃ አማራጮችን፣  የመስኖ ቴክኖሎጂዎችንና  የተለያዩ ግብአቶችን የመጠቀም ፍላጎት እየተሻሻለ መምጣቱን የገመገመው ስራ አስፈፃሚ  ኮሚቴው በዘርፉ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን የተቻለው ምልአተ-ህዝቡን ማሳተፍና ማነቃነቅ  በመቻሉ ነው ብሏል ኮሚቴው።

በየደረጃው ያለ አመራር ተቀናጅቶ ከየአካባቢው የተገኙ መልካም አፈፃፀሞችን ወደሁሉም አካባቢዎች የማዳረስና   በመስኖ ልማት የተደራጀ የልማት ሰራዊት የመገንባት ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚቴው  አቅጣጫ ማስቀመጡን መግለጫው ጠቁሟል።

በገጠር ስራ ፈላጊዎችን ወደ ስራ ለማሰማራት እንዲቻል በየአካባቢው የሚገኙ የስራ ዕድሎችንና የስራ ፈላጊዎቹን ፍላጎት በዝርዝር የማጥናት፣ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችን የማዘጋጀት እንዲሁም የመስሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ስራዎች በተሻለ ሁኔታ መፈፀማቸውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ልማት ረገድም በአብዛኛው አካባቢዎች የዝግጅት ስራዎች በአግባቡ ተጠናቀው ወደ ስራ መገባቱንና በላቀ የለውጥ ሰራዊት ንቅናቄ ለመፈጸም ርብርብ እተደረገ መሆኑን ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

መግለጫው አይይዞም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም በማጠናከርና የታላቁን ህዳሴ ግድብና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በዘላቂነት ከማልማት አኳያ ከፍተኛ  ፋይዳ ያለው በመሆኑ በላቀ ደረጃ የሚፈፀምበትን አግባብ አመላክቷል፡፡

ሁሉንም  የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በመለየትና  አስፈላጊውን የበልግ ዝግጅት ስራ በመፈፀም በኩልም የተሻሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ ኮሚቴው መገምገሙን መግለጫው ያሳያል።

በፌደራል፣ በክልሎችና በአዲስ አበባ የመልካም አስተዳደር ተግባራዊ እንቅስቃሴን በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን መልካም አስተዳደር የማስፈን ትግሉ ማጠንጠኛ  የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በማዳከምና በማድረቅ የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ማረጋገጥ ነው መሆኑን አስምሮበታል።

የትግሉ መሰረታዊ ግብ የተጠያቂነትና ግልፅነት አሰራሮችን በማጎልበት የህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥቶ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተወያይቷል።

መልካም አስተዳደር የማረጋገጥ ስራ በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ የሚፈፀም ከመሆኑ አንፃር በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ አሉ የሚላቸውን የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችና ብልሹ አሰራሮች በግልፅ ማቅረብ የሚያስችሉት መድረኮች እንደተፈጠሩ የገመገመው ኮሚቴው   ሂደቱም ለቀጣይ ስራ የሚያግዙ  መልካም ልምዶችና ስኬቶች የተገኙበት እንደሆነም አረጋግጧል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች በየደረጃው ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በማደራጀት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት ላይ መሆኑንም አይቷል፡፡

የመልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት በእስካሁኑ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ቢሆንም አሁንም የህዝብን እርካታ በማረጋገጥ ረገድ የሚታዩ እጥረቶችን በማረም ቀጣይነት ያለው የተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት የሚጠበቅባቸውን ህዝባዊ አገልግሎቶች ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በተጠያቂነት መንፈስ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባችው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን መግለጫው ያሳያል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡