አዲስ አስተሳሰብ ለለውጥ

Normal 0 false false false EN-US X-NONE X-NONE

/* Style Definitions */
table.MsoNormalTable
{mso-style-name:”Table Normal”;
mso-tstyle-rowband-size:0;
mso-tstyle-colband-size:0;
mso-style-noshow:yes;
mso-style-priority:99;
mso-style-qformat:yes;
mso-style-parent:””;
mso-padding-alt:0in 5.4pt 0in 5.4pt;
mso-para-margin-top:0in;
mso-para-margin-right:0in;
mso-para-margin-bottom:10.0pt;
mso-para-margin-left:0in;
line-height:115%;
mso-pagination:widow-orphan;
font-size:11.0pt;
font-family:”Calibri”,”sans-serif”;
mso-ascii-font-family:Calibri;
mso-ascii-theme-font:minor-latin;
mso-fareast-font-family:”Times New Roman”;
mso-fareast-theme-font:minor-fareast;
mso-hansi-font-family:Calibri;
mso-hansi-theme-font:minor-latin;
mso-bidi-font-family:”Times New Roman”;
mso-bidi-theme-font:minor-bidi;}

አለሙ

ብዙዎች የሃገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ሲቃረብ በከተማና በገጠር ሽርጉድ ያበዛሉ፡፡በአግባቡ ቢሆን ኖሮ ለምርጫ መዘገጃጀቱ ባልከፋ ነበር። ዳሩ ከወዲሁ የተለመደውንና የሰለቸውን ዓይነት ጭፍን ተቃውና ውግዘት፣ሃሰተኛ ክስና ውንጀላ የፓርቲ ፕሮግራማቸውና የምርጫ መለያቸው እስኪመስል ድረስ እንደ አዲስ መልሰው መላልሰው በየግሉ ሚዲያ ያንበለብሉታል እንጂ፡፡ በባሕርማዶም ጥቂት አጫፋሪዎቻቸው ጩኸታቸውን ያስተጋቡላቸዋል። ለጊዜው እርስ በእርስ ይወዳደሳሉ፣አንዱ ደካማ የባሰበትን ሌላውን ደካማ ደጋግፎ ለማቆምና ዳዴ ለማስባል ይውተረተራል፣ትንሽ ቆይተው ደግሞ እርስ በርሳቸው ይወነጃጀላሉ፣አንዱ ራሱን “ሃቀኛ” ሌላውን”አስመሳይና ተለጣፊ” በማለት ይዘልፋል፣ይወርፋል፡፡ አንዱ “አባራሪ” ሌላው “ተባራሪ” እስኪመስሉ የአዳራሽ ውስጥ ፖለቲካዊ ትወናቸውን በጥላቻ አጅበው ያጠናቅቁና በሌላ ዙር ከርሞ እንገናኝና ያኔ ይለይልናል ይባባላሉ። የአንድ ፓርቲ መሪ በራሱ አለያም “ህብረት” ወይም “ጥምረት” ወይም “ውህደት”ፈጠሩ የተባሉ ሆኖም እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ፓርቲዎች ተወካዮች በዋሸንግተን፤ ኒውዮርክ፤አትላንታ፤ጆርጅያ፤ለንደን፤ቦን…ወዘተ ስብሰባ ጠርተዋል ይባላል። ከሁለት አሰርት ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ያለ ይመስል ዲስኩሩ በአዳራሽ ይቀደዳል፣ እምቢልታው ይነፋል፣ ከበሮው ይደለቃል፣ክተት ይታወጃል።

መንግሥትን በሃሰት በመወንጀልና በመክሰስ፣የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሃገራት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጡትን ማንኛውንም የልማት ዕርዳታና ብድር እንዲያቋርጡ ምዕራባውያንን ተንበርክከው በመማጸን ድጋፍ ለማሰባሰብ ይሯሯጣሉ። ለምን? ተብለው ሲጠየቁ ምርጫ የሚሉት የትርፍ ጊዜ ሥራ ከፊታቸው ተደቅኗላ፣ይህን ካላደረጉስ የሚኖሩበት ሃገር መንግሥትና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ነን የሚሉትን ሰዎች እንዴት አድርገው “ከነክብራቸውና ግርማ ሞገሳቸው” ይወቋቸው? ይህም እኮ ቢሆን ለእነርሱ የተፈጥሮና የሶሻል ሳይንስ ምሁርና ተመራማሪ፣ የስፖርት ሰው አለያም የኪነጥበብ ባለሙያ ወዘተ ሳይሆኑና ሳይደክሙ ዕውቅና ለማግኘት አንዱ አቋራጭ መንገድ መሆኑ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጀ ይባልና ከዚያ ከፈረደበት ዲያስፖራ ዶላር ለማሰባሰብ ሽር ጉድ ይባላል። ከእርዳታ ገንዘቡ ከፊሉ ወደ አገር ከገባም መታደል ነው፡፡ የገባውም ቢሆን ከዚህ በፊት በተግባር እንደታየው የዋና አለቆቹ መጠቀሚያ ከመሆኑ ውጭ በትክክል ለታለመበት ዓላማ ሥራ ላይ ስለመዋሉ በእጅጉ አጠራጣሪ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ውስጠ አዋቂዎች እንደሚሉት ጠያቂም፣ ተጠያቂም የለ፡፡ ይህን የሚጠራጠር ካለ የገንዘብ አሰባሰባቸውን፣አያያዛቸውንና አወጣጣቸውን በተመለከተ የሂሳብ መዛግብቶቻቸውንና “ሪፖርታቸውን” በቅርበት ከሚያውቁ አባሎቻቸው በግልጽ መረዳት እንደሚቻል ብዙዎች ይናገራሉ። ለነገሩ ይህ እንኳ በእርግጥ የራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ስለሆነና ከዚህ ጽሁፍ ዓላማ ጋር ስለማይያዝ በዚሁ ልለፈው።

አጋፋሪዎቻቸውም ከውጭ ገንዘብ ያላዋጣላቸውን በዘመኑ አባባል“ያጠቁሩታል- ያስጠቁሩታል”፣ ያለ ስሙ-ስም ይለጥፉበታል፣ ከማህበራዊ ሕይዎት እንዲገለል ይቀሰቅሱበታል፣እነርሱ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዙ ወደ ሃገር ቤት መግቢያውን ይጠብቅ ይባላል፣አገሩ አሜሪካና አውሮፓ ሆነ እንጂ ከዚህም አልፎ የቀንና የሌሊት ፋኖዎችን በማደራጀትም ሊያሳድዱት ይችላሉ። ይህን ዓላማችሁን ስለማንቀበለውና ስለማናምንበት አንደግፋችሁም ብለው በግልጽ በተቃወሟቸውና ባወገዟቸው አለያም በማንኛውም የፖለቲካ ጉዳይ መግባት አንፈልግም፣ገለልተኛ ነን ባሏቸው በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ተከስቶ ያየነውና ብዙዎች የገፈቱ ቀማሾች በአደባባይ የተናገሩት ሃቅም ይህ ነው። አስፈላጊ አይሆንም እንጂ ሥም ጠርቶ ሕያው ምስክርነታቸውን እዚህ ላይ ማቅረብ ይቻል ነበር።

የአዲስ አበባው ተቃዋሚ መሪም ቪዛ አስመትቶ በአብዛኛው ወደ አሜሪካና አውሮፓ የሚሄደው የዶላር መዋጮ ለመሰብሰብ ነው፡፡ ባለጉዳዩ ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለው ኢትዮጵያ እንጂ ውጭ ሃገር አይደለም፡፡ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳ በዋናነት የሚቀረጸው፤መርሀ ግብር የሚወጣው፤የሚሻረው ወይንም የሚጸድቀው በቀጥታ በዋነኛው ህዝብ ሳይሆን በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀው በሚገኙና የአገሪቱን ተጨባጭ እውነታ በስማ በለው ብቻ በሚያውቁት፤አለያም ሆን ብለው በሚያደናግሩ ከሀገር ከወጡም በርካታ አስርት አመታት ባስቆጠሩ ጥቂት የዲያስፖራ ፖለቲከኞች የሆነው፡፡ በመሰረቱ ውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ በሃገሩ ጉዳይ የመነጋገር፣የመምከር፣የራሱን ገንቢ ሚና የመጫዎት ሙሉ መብት ያለው ስለመሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይሆንም።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች መሰረታቸውን የተከሉት በአገር ቤት ባለው ህዝብ ላይ ሳይሆን በዲያስፖራ ፖለቲከኞች ላይ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የውጭ ሀይሎችን ተስፋ አድርጎና ተማምኖ ለስልጣን ያበቁኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡ መሰረቱን ህዝብ ያላደረገ ፖለቲካ፤በራሱ ህዝብ ሳይሆን በውጭ ሀይሎች የሚተማመንና የሚመካ የፖለቲካ ድርጅት ምንጊዜም ቢሆን ውጤት ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ቅንጅቶች ታስረው በይቅርታ ሲፈቱ በአገር ውስጥ ያለውንና ዋጋ ያስከፈሉትን ህዝብ አላነጋገሩም፣ይቅርታም አልጠየቁትም፡፡ ውለው ሳድሩ በየተራ ሁሉም አሜሪካና አውሮፓ ነው የተጉዋዙት፡፡ በመሀላቸው ለተፈጠረውም መከፋፈል ጉዳያቸውን ለሽምግልና ያቀረቡትና ዳኝነት የጠየቁት ዲያስፖራውን እንጂ ሃገር ውስጥ ያለውን ደጋፊያቸውን ወይም የኢትዮጵያን ህዝብ አይደለም፡፡ ታድያ ህዝቡን ምን አድርግ ነው የሚሉት? በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ተቃዋሚዎችና ጽንፈኞች ዘንድ ዲሞክራሲ ከወሬ ያለፈ ሲተገበር አይታይም። አያውቁትም፡፡ ምክንያቱም እነርሱን መቃወም፤መተቸት፤መውቀስ አይሞከርም፣ሌላ ሥም ያሰጣል፡፡ ሂስና ግለሂስ፤ዲሞክራሲያዊ አሰራር፤የግለሰብንና የቡድንን መብት ማክበር ከየት ያምጡት፡፡ እብሪተኝነት፤ማንአለብኝነት፤ስሜታዊነት፤አምባገነንነት የመሪዎቹ ዋነኛ መለያ ነው፡፡

ለሰብአዊ መብትና ክብር ቅንጣት ከበሬታ የሌላቸው አክራሪዎች የግለሰብን ስምና ክብር እንዳሻቸው ከማጉደፍ፤ከመሳደብና ከማጥላላት ውጭ ጨዋነት ለእነሱ ቦታ የለውም፡፡ ወቅትና ዘመን የማያስተምራቸው፤ከህዝብም ከታሪክም ለመማር ያልቻሉ፤ለመማርም ፈቃደኝነቱ የሌላቸው፤ሁነው ህዝብንና ልጆቹን ዋጋ እያስከፈሉ፤ አንዳንዶች ባህር ማዶ በምቾትና በድሎት ተንቀባረው ይኖራሉ፡፡ልጆቻቸውንም በምርጥ ኮሌጆችና ዩኒበርሲቲዎች ያስተምራሉ፡፡ እዛ ሁነው አገር ቤት ያለውን ህዝብ ለሁከትና ትርምስ ሊያሰልፉት ይማስናሉ፣የችግሩ ወላፈን የት ሊደርስባቸው ያሳስባቸዋል፡፡

ከእኔ የተለየ አመለካከትና የፖለቲካ አቋም ያለው ሁሉ ጠላት ነው፤ የሚለው የዲሞክራሲ ባህልን የሚገድል መርዘኛ በሽታ የአንዳንድ ተቃዋሚ ሀይሎች አይነተኛ መለያ መሆኑ የሚያሳዝን ነው። እነሱ ብቻ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አሳቢ፣ ተቆርቋሪ፤ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ፤ ሌላው ከሀዲ፣ አድርባይ ለሀገሩ የማይቆረቆር፣ የማይጨነቅና የማያስብ ነው ብለው ደምድመዋል፡፡ ከዚህ ክፉኛ ከተጣባቸው ጸረ- ዲሞክራሲ አስተሳሰብ እስካለተላቀቁ ድረስ ሕዝብን ይመራሉ ብሎ ማሰብ ከእባብ እንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው፡፡ አደጋውም በእጅጉ የከፋና አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

በየትኛውም የዓለም ታሪክ መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች ስለሃገራቸውና ሕዝባቸው በጥሩም ይሁን በመጥፎ ጎኑ ሊወሰድ የሚችል የራሳቸው ራዕይ ነበራቸው፣ይኖራቸዋል ተብሎም ይታሰባል ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይን ከታላቁ ናፖሊዮን ቦናፓርት፤ ጀርመንን ከቢስማርክ፤ እንግሊዝን ከዊንስተን ቸርችል፤ ቱርክን ከመስራቿ ከከማል ፓሻ አታቱርክ፤ ቻይናን ከማኦዜዱንግ፤ሩሲያን ከሌኒን፤ ቪየትናምን ከሆቺማን፤ ደቡብ አፍሪካን ከኔልሰን ማንዴላ ራዕይ፤ወዘተ ጋር በማያያዝ መመልከት ይቻላል። ሁሉም ሃገራት እንደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ተመሳሳይ ነገር ይኖራቸዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ከግዜ ሂደትና ለውጥ እንዲሁም የእድገት ሕግ አንጻር የቀደመው ራዕይ በተሻለ ራዕይ ሊተካ ይችላል፡፡ ሕዝቦች የታላላቅ መሪዎችንና ሞዴሎቻቸውን ራዕይ እያሳኩ ለውጡን ሲያጣጥሙ ባለውለታነታቸውን እያደነቁና እየዘከሩ ያስታውሳሉ፡፡ ሰዎቹ ቢያልፉም ራዕያቸው ወደ ትውልዱ ይሸጋገራል፡፡ የእኛዎቹ የጨለማና የድንቁርና አስተሳሰብ የፈነጨባቸው አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጀቶችና ምሁር ነን ባዮች ስለ መለስ ራዕይ ሲነገር “በሙት መንፈስ የምትመራ” ሀገር ሆነች ይሉናል። ይህን የወረደና የዘቀጠ አስተሳሰብ መስማት የድርጅቶቹንና የመሪዎቹን ማንነት በገሀድ ያሳያል፡፡ እነሱማ እንኩዋን ለሀገርና ብሎም ለአፍሪካ የተረፈ ግዙፍ ራእይ ቀርቶ ለራሳቸው የበቃና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መተዳደሪያ ህገ ደምብ፤ ከዚያም አለፍ ሲል በግልጽ የተቀመጠ፣ሕዝብ ያወቀውና የተወያየበት ስትራቴጂና ፕሮግራም /መንግሥትን ማብጠልጠላቸውንና በሃሰት መክሰሳቸውን እንደ ፕሮግራም ካለቆጠሩት በስተቀር\ እንደሌላቸው በውል የታወቀ ነው፡፡

ጽንፈኛው ተቀዋሚ ሀገርን የማሳደግ ራዕይ ሳይሆን ያለው ሀገርን የማመስና የማተራመስ አጀንዳ ነው ያለው፡፡ ይልቁንስ መለስ ኢትዮጵያን የበለጸገች፤ ተሰሚና ተደማጭ ሀገር እንድትሆን የከፈለው መስዋትነትና ኢህአዴግን በግምባር ቀደምትነት በመምራት ያስቀመጠው ሃገራዊ ራዕይ ለኢትዮጵያ እድገት ይበጃል፤ ከድህነትና ከተመጽዋችነት ያወጣናል ብሎ በማመኑ ሕዝቡ የተያያዘውን ልማት ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

ተቃዋሚው ለሀገርና ለሕዝብ እቆረቆራለሁ እስካለ ድረስ ሀገርን ከማልማት፣ ከማሳደግና ክብሯን ከማስጠበቅ ውጭ የተለየ ራዕይ አለው ማለት ነው? በጥላቻ የተሞላ፣ በስሜታዊነት የነበዘ፤ ለሀገርና ለወገን እድገትና ልማት የሚጠቅመውን እንኳን በቅጡ ለይቶ ያላወቀ፤ ራዕይ የሌለው፤ በሌላ በኩል ሁሉንም ነገር መቃወም የስልጣኔና የእውቀት መገለጫ ነው ብሎ የሚያምን እስከሆነ ድረስ ለሕዝብና ለሃገር አንዳች ረብ ያለው ውጤት ያስገኛል ተብሎ እየጠበቅም።

አበው “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር” እንዲሉ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሰከን ብለው ከጭፍን ጥላቻና ካልሰለጠነ ፖለቲካዊ አካሄድ እስካልወጡና በተግባርም ለውጥ እስካላመጡ ድረስ እነርሱን ተስፋ ማድረግ “ጥቁር ወተት” የማለም ያህል ስለሚሆን ውጤቱ የሚያምር አይሆንም። እናማ ሀገርን መምራት እነርሱ እንደሚያወሩትና እንደሚቃወሙት ቀላል አይሆንምና ለሁሉም እየተስተዋለ የሚለው መልዕክቴ ነው፡፡