በግማሽ የበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል ከቤንዚል ጋር በማደባለቅ አገልግሎት ላይ መዋሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2006/ዋኢማ/- በግማሽ የበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ኢታኖልን ከቤንዚል ጋር በማደባለቅ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ማዳን መቻሉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ባለፉት ስድስት ወራት የተመረተው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል በነባር የስኳር ፋብሪካ በሆኑት በፊንጫና በመተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ነው።   
የባዮ ኢታኖል ምርት በሁለት ነባር ስኳር ፋብሪካዎች የሚመረት መሆኑን የገለፁት አቶ ብዙነህ፤ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በዓመት እስከ 20 ሚሊየን ሊትር የሚያመርት ሲሆን፤ የመተሃራ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራል ብለዋል።
በአጠቃላይ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት ከ10 ያላነሱ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንደሚገነቡ ጠቁመው፤ በ2007 ዓ.ም እስከ 181 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል ማምረት እንደሚቻልና 64 ነጥብ 4 ሚሊየን ሊትሩን ከቤንዚል ጋር በማደባለቅ በአሁኑ ገበያ ዋጋ እስከ 57 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።
እንዲሁም 25 በመቶ ኢታኖልን ከ75 በመቶ ቤንዚል ጋር ማደባለቅ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ብዙነህ ገልፀዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ከ5 በመቶ እስከ 10 በመቶ ኢታኖል የማደባለቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ ከ10 በመቶ በላይ ለማድረስ ግን መኪናዎችን የማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል  ብለዋል።
ኢታኖልን ከቤንዚል ጋር የማደባለቁ ስራ ጥቅምት 2001 ዓ.ም መጀመሩን የገለፁት አቶ ብዙነህ የማደባለቁ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን 41 ነጥብ 77 ሊትር ኢታኖል ከቤንዚል ጋር ማደባለቅ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም ከ33 ነጥብ 23 ሚሊየን ዶላር በላይ ለቤንዚል ይውል የነበረ የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደተቻለ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግባ ያስረዳል።