የደቡብ ሱዳን ግጭት ተዋናዮች የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ጥር 16/2006 (ዋኢማ) – በደቡብ ሱዳን በተነሳው ግጭት ተሳታፊ የሆኑት ወገኖች  የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ።
ትናንት በአዲስ አበባ በቀጠለው ድርድር ሁለቱ ወገኖች እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ነው በ24 ሰዓታት ውስጥ ተኩስ ለማቆም ስምምነት የተፈራረሙት።
በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/በኩል ድርድሩን በሊቀመንበርነት በሚመሩት አምባሳደር ስዩም መስፍን አደራዳሪነት ሁለቱ ወገኖች ሲደራደሩ ቢቆዩም፥ በትናንትናው ዕለት ነው ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ መድረስ የቻሉት።
በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አደሃኖም ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
በእስካሁኑ ግጭትም ከ70 ሺህ በላይ በሱዳን  የሚገኙ ዜጎች ተፈናቅለዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)