በህወሓት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዙሪያ እነማን ምን አሉ?

በሰለሞን ሽፈራው
(ክፍል አንድ)

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ከኢህአዲግ አባል ድርጅትቶች የአንጋፋነቱን ስፍራ እንደሚይዝ ይታወቃል። የዚያኑ ያህልም ለኢህአዲግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቶና ትግል መሳካት የፋናወጊነት ሚና የተጫወተና እየተጫወተ የሚገኝ ድርጅት ነው ህወሓት።

ከዚህ የተነሳም ኢህአዴግንና እርሱ የሚመራውን ፌዴራላዊ መንግስት “በአንድ ወይም በሌላ መልኩ” የማስወገድ አላማ ያላቸው ጽንፈኛ ተቃዋሚ  የፖለቲካ ፖርቲዎች ህወሓትን በተለየ የጠላትነት መንፈስ እንደሚመለከቱት ይታመናል። ምክንያታቸው ደግሞ በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የጀመሩትን የስርነቀል ለውጥ ጉዞ  ለመቀልበስ የሚደረገውን ሙከራ ሁሉ በማክሸፍ ረገድ የህወሓት አመራር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ስለሆነም አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትመራበትን ሕገ መንግስታዊ ስርአት ለመደርመስና የስርነቀል ለውጥ ጉዞውን ቀልብሰው በትረ ስልጣን ለመጨበጥ የሚፈልጉ ሃይሎች የሚያካሒዱት ፀረ ኢህአዲግ የተቃውሞ እንቀስቃሴ በተለይም ህወሓት ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ፖለቲካን መሠረት ያደረገ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

እናም በእኛ ሀገር የሚገኙ አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበት ተመሳሳይ ባህሪ ቢኖር እነርሱ “የኢህአዲግ አስኳል” የሚሉት ህወሓት ተቀባይነት እንዳያገኝ ወይም ከህዝብ እንዲነጠል ለማድረግ  ያለመ አሉባልታና የበሬ ወለደ አይነት ውዥንብር በማናፈስ ላይ የሚጠመዱ የመሆናቸው  ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ “ህወሓት እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ህልውናውን እንዲያስቀጥል አንፈቅድለትም ” የሚል ጽፀፈኛ አቋም ያላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸውን አውቃለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓትን ልክ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚቆጥሩትና በእልፍ ኣላፍ የትግራይ ህዝብ ልጆች መስዋእትነት የተገነባ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ስለመሆኑ የሚናገሩ ወገኖች የመኖራቸው ጉዳይ የሚያከራክር አይደለም። ያም ሆነ ይህ ግን ከኢህአዲግ አባል ድርጅቶች መካከል የአንጋፋነቱን ቀዳሚ ስፍራ የሚይዘው የህወሓት 40ኛ ዓመት የምሰረታ በዓሉን ሲያከብር የተስተዋለው እውነታ የድርጅቱን አቋምና እንዲሁም በህዝብ ዘንድ የሚሰጠውን ቦታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ያደረገልን ይመስለኛል።   

ባለፈው የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በተለየ ድምቀት የተከበረውን የህወሓትን 40ኛ ዓመት  የምስረታ  በዓል ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች በጉዳዩ ዙሪያ የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰነዝሩ መደመጣቸውም ያለምክንያት አይደለም። ይልቁንስ ድርጅቱ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘላቂ እጣ ፈንታ መቃናት የተጫወተውን ታሪካዊ ሚና የሚመጥን ስፋትና ጥልቀት በተላበሰ ዝግጅት የተከበረው የህወሓት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ለቀጣዩ ፀረ ድህነት ትግል ይበልጥ የመነቃቃት መንፈስ ስለፈጠረ እንጂ።

ሁኔታው የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ጭምር እንደመሆኑ መጠንም የጽንፈኝነት አባዜ የተጠናወተውን የተቃውሞ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ሃይሎችን ክፉኛ አስደንግጧቸዋል። ከመደንገጣቸው የተነሳ የተለመደውን ጭፍን ጥላቻ የተጠናወተው አሉባልታ ይበልጥ በወረደ መልኩ ሲያናፍሱ መሰንበታቸውን መረዳት የሚቻለው በተለይ ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚጽፉትን እንቶ ፈንቶ በማየት ነው።  ደግነቱ ግን ዛሬም ለእነርሱ የበሬ ወለደ ውዠንብር ቦታ የሚሰጥ ህብረተሰብ እንደሌለ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

ስለዚህም የህወሓት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የተከበረበት ልዩ ድምቀት ያስደገነጣቸው ጽንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክራሪዎቹ ዲያስፖራዎች ደጋፊዎቻቸው የሚያናፍሱትን ከተስፋ መቁረጥ ስሜት የመነጨ ተራ አሉቧልታ ወደ ጐን ትተን ለህወሓት መራሹ የትግራይ ህዝብ ፀረ ጭቆና ትግል ጤናማ አመለካከት ያላቸው ወገኖች በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡንን አስትያየት እናካፍላችሁ።

በዚህ ፅሁፍ የተካተቱት አስተያየት ሰጭዎች በአሉን ለማክበር በመቐለ ስታዲዮም ከታደመው ህዝብ መካከል መርጠን ያነጋገርናቸው ሲሆኑ ስብጥራቸውም የመጡበትን የህብረተሰብ ክፍል ግምት ውስጥ ያስገባ የሃሳብ ተዋጽኦን መሰረት ያደረገ ነው። እንግዲያውስ የህወሓትን 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር ሲሉ ባህር ውቂያኖሱን አቋርጠው ከአውሮፖና ከአሜሪካ ጭምር የመጡትን ዲያስፖራዎች ይወክልልናል ያልኩትን እንግዳ ላስቀድም …

ከሀገረ ጀርመን  የመጣው  አቶ  አብዱ  በጉልምስና  የእድሜ  ክልል የሚገኝ የትግራይ ተወላጅ ሲሆን በዘንድሮው የየካቲት 11 በዓል ላይ ባለቤቱና ልጆቹ  ባለመገኘታቸው የተሰማውን ቁጭት በመግለጽ ነው ጨዋታውን  የጀመረልኝ፡፡ የቁጭቱን  ምክንያት  ሲያብራራም  “እስቲ  ይህን ታጋይ  ህዝብ  ተመልከተው? ልጆቼ  ከእኔ ጋር መጥተው ቢሆን ኖሮ ትግራዋይነት ምን ማለት እንደሆነ በተሻለ መልኩ ለመረዳት የሚያስችል እውቀት ያገኙበት  ነበር ከበዓሉ  አጠቃላይ  ድባብ። እውነት  ለመናገር  ስለ ማንነነቴ  የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረኝ አድርጐልኛል የህዝቡ ሁኔታ” ይላል ዲያስፖራው አቶ አብዱ።

እንደርሱ በምእራቡ አለም ሀገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ለህወሓት ያላቸው አመለካከት ምን እንደሚመስል ይገልጽልኝ ዘንድ ጠይቄው የሰጠኝ ምላሽ ደግሞ ይሄውላችሁ “ብታምንም ባታምንም ህወሓትን የሚጠላ የትግራይ ተወላጅ ዲያስፖራ የለም ልልህ እችላለሁ” ይህ ማለት ደግሞ ድርጅቱ በእልፍ አላፍ የትግራይ ህዝብ ልጆች መስዋእትነት የተገነባ እንደመሆኑ መጠን እኛ ዲያስፖራዎችም በያለንበት የስደት አለም ሆነን ህወሓትን ከመደገፍ አንቦዝንም ልልህ ፈልጌ ነው።

በተለይም ደግሞ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚያራምዱት በለየለት ጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ጽንፈኛ አቋም እየተባባሰ መምጣቱን ስንመለከት ህወሓት ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ሌላ ምርጫ እንደሌለ ነው አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ ዲያስፖራ እርግጠኛ የሆነው። ስለዚህ አሁን ድርጅቱ ያለበት ቁመና ኩራት እንዲሰማን ማድረጉን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከህወሓት /ኢህአዲግ ጋር መጭው ዘመን ብሩህ የማይሆንበት ምክንያት እንደማይኖርም ከወዲሁ መገመት ይቻላል” ብሏል አቶ አብዱ። የሌሎቹን እንግዶቼን አስተያየት በክፍል ሁለት ጽሑፌ ይዤ እንደምመለስ እየገለጽኩ ለዛሬው ግን  እዚህ ላይ ላብቃ።