በያዝነው ወር ኢትዮጵያ የኮሜሳ ሊቀመንበርነት ስፍራን ትረከባለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/ 2007 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ የምስራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ ኮሜሳን የሊቀመንበርነት ስፍራ በያዝነው ወር ትረከባለች።

18ኛው የኮሜሳ የመሪዎች ጉባኤ ከመገቢት 11፣ 2007 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው “ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት” በሚል መሪ ቃል ነው የሚካሄደው።

በጉዳዩ ዙሪያ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ድኤታ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መድረኩ ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፥ በበርካታ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

ኢትዮጵያም  በዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ያላትን ተሞክሮዎች ለአባል ሀገራቱ ለማካፈል ትጠቀምበታለች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኮሜሳ የፕሬዚዳንትነት ስፍራን ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ይረከባሉ ተብሎም ይጠበቃል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)