የፖለቲካ ፓርቲዎች የፊት ለፊት ክርክር አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5/ 2007 (ዋኢማ) – የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመሪያ የፊት ለፊት ክርክር ዛሬ ተጀምሯል።

በዛሬው እለትም 5 ፓርቲዎች የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በኢትዮዽያ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ነው ክርክር ያካሄዱት።

የተከራከሩት የኢትዮዽያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ፣ የኢትዮዽያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ/መድረክ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ እና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው።.

በክርክሩ ላይ ፓርቲዎች በመከራከሪያ ሀሳቡ ላይ የአማራጭ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ እድል ተሰጥቷቸዋል።

መድረክ በክርክሩ ላይ “አሁን ኢህአዴግ አለ የሚለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያላሟላ በመሆኑ
በአገሪቱ ከአንድ በላይ ፓርቲም የለም” ብሏል።

በዚህም ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ “በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች የሌሉበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲል ገልጿል።

ፓርቲው “ዜጎች ሀሳባቸውን የመግለፅ እና ተዘዋውረው የመስራት መብት የላቸውም” ሲል ሀሳቡን አቅርቧል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በበኩሉ “በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ማካሄዱ ዴሞክራት አያስብልም፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብት በአግባቡ እየተመለሰ አይደለም፤ ይልቁንም ኢህአዴግ ከፋፍሎ ለመግዛት እየተጠቀመበት ነው” የሚል ማብራሪያን ነው የሰጠው።

በ21 የተለያዩ ዘርፎች አማራጭ ፖሊሲዎችን እንዳቀረበ የሚገልፀው አዲስ ትውልድ ፓርቲ “የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም ሶሻሊስታዊ እና አፋኝ ስርዓት ነው” የሚል ሀሳብ አስደምጧል።

“ፓርቲው በአገሪቱ አመጣኋቸው የሚላቸው የልማት ስዎች በኪሳራ ላይ የተመሰረቱ፤ ዛሬ ፈርሰው ዛሬ መገንባት ላይ የተመሰረቱ ናቸው” ብሏል።

ኢህአዴግ “የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኛ ብንሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ የምናመጣው ይህ ነው የሚል አማራጭ ማቅረብ አልቻሉም” ሲል ወቅሷል። “እኛ ብንመረጥ ልማትን በዚህ መልኩ እናመጣለን ከማለት ይልቅ የሰው ሀሳብ የሚተቹም ናቸው” ብሏል።

“የፖለቲካ ፓርቲዎችን ኢህአዴግ እየደገፈ እና እየኮተኮተ ሊያጠነክራቸው አይችልም” ያለው ፓርቲው፥ “ሊያጠንክራቸው የሚችል ህግ እና ሜዳ ግን መኖሩን አነስቷል።

“ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መኖር በዘንድሮው ምርጫ በክርክሩ የተሳተፉትን ጨምሮ 57 ፓርቲዎች መሳተፋቸው በቂ ነው” ብሏል።

“ፓርቲዎቹ የማይጠነክሩበት ምክንያት ህዝባዊ መሰረት ስለሌላቸው፣ የየትኛውንም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ የሚመልስ መፍትሄ ስለሌላቸው ነው” ብሎ ተከራክሯል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ በላይ ፓርቲ የለም በሚል ከመድረክ የቀረበው መከራከሪያ ራስን መካድን ያካተተ ነው” ብሏል።

ድክመታቸው ውስጣቸውን አለማየት መሆኑን በማንሳትም “ልዩነትን የሚያስተናግድ የውስጥ ዴሞክራሲ እጦት ነው እያንዳንዱ ፓርቲ ለሁለት መከፈሉ ማሳያ ነው” ሲል ገልጿል።

“ሰማያዊ ፓርቲ ይህን ምርጫ ህዝብ ይመርጠኛል ብሎ ሳይሆን ፓርቲው ለዴያስፖራው ገብቶ የመጣውን ቃል ለመጠበቅ ለሁከት መንደርደሪያነት እየተጠቀመው ነው” ሲል ተናግሯል።

በአጠቃላይ ዴሞክራሲ፣ ሰላም እና ልማት ለኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች ናቸው ብሎ እንደሚያምንም ነው ያስታወቀው።

“ብዘሃነትን መቀበል እና እንደሰው እኩል መሆናችንን ማረጋገጥ ችሏል፤ ይህንንም መብት በህገመንግስት ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል” ብሏል።

ዛሬ ላይ የዜጎች የሀሳብ ነፃነት የግለሰብ መብቶች መረጋገጣቸውን በመግለፅም፥ በማሳያነት 21 የማህበረሰብ ሬዲዮኖች፣ ከ20 በላይ የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች መከፈታቸውን እና 10 ሺህ መፅሃፍት መታተማቸውን አንስቷል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)