ሕገ መንግሥታዊ አስተምህሮ!

ከህዳር 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ ደጋግሞ ሲጎበኘን በተስተዋለው ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት የአገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ይበልጥ ተጋግሎ መቆየቱ የሚካድ አይደለም፡፡ አሉታዊው ክስተት ከመደጋገሙ የተነሳ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ለአሳሳቢ የቅልበሳ አደጋ የተጋለጠ የሚያስመስል አዝማሚያ የተስተዋለባቸውን አጋጣሚዎች እስከ መታዘብ መድራሳችንም የሚታወቅ      ነው፡፡

እናም ያንን አደገኛ አዝማሚያ የተስተዋለበት ሁከት ተከትሎ ይበልጥ በተጋጋለው ፖለቲካዊ ትኩሳት ውስጥ ጎልቶ ሲደመጥ የሰነበተውን አስተያየት እንደታዘብኩት፤ሕገ መንግስታዊ አስተሳሰብን የማስረጽ አስፈላጊነት ተገቢ ትኩረት ሳይሰጠው በመቅረቱ ምክንያት ሥርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ክስተቶች መደጋገማቸውን የሚያመለክት ትችት የተሰነዘረበት አግባብ ነበር፡፡ በተለይ፤ አንዳንድ የተቃውሞው ጎን ፖለቲከኞች፤ ኢህአዴግ ሕገ መንግሥት ቀርጾ ቢነሳም ሕገ መንግሥታዊነትን ሊያሰፍን አልቻለም›› ሲሉ የሰላ ትችታቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጽፈው እንዳነበቡን ማስታወስ አያዳግትም፤፤

ለነገሩ ከዚህ አኳያ የሚቀርበውን ነቀፌታ ኢህአዴግና መንግስትም ጭምር ለማስተባበል እንደማይሞክሩ፤ ወይም የችግሩን መኖር አምነው እንደሚቀበሉ የሚያመለክ አንድምታ ያዘለ ሃሳብ ነው በተለያዩ  የገዥው ከፍተኛ የፓርቲ አመራር አካላት አንደበት ሲገልጽ የሰማሁት፤ ለምሣሌ፤ የፌደራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፤ እንዲሁም አቶ ዛዲግ አብርሃን የመሳሰሉት የኢህአዴግ ሰዎች ለፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት የውይይት መድረኮች ላይ የሰጡትን አስተያየት ማስታወስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንደእኔ እምነት ከሆነ ሕገ መንግሥታዊ እሳቤን ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት የማስረጽ አለማስረጽ አስፈላጊነት እንብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ከመቆየቱ የተነሳ አሁን አሁን በሥርዓቱ ላይ ተደጋግሞ ሲቃጣ የሚስተዋለው የቅልበሳ አደጋ እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመለክት አስተያየት ሲሰነዘሩ የሚደመጡት ወገኖች የሚያቀርቡት ሃሳብ ተገቢነት ያለው ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡

ምክንያቱም፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአገራችንን ነባራዊ እውነታዎች በቅጡ እያገናዘበ ስለመረቀቁና ስለመጽደቁ እንደዋነኛ ማረጋገጫ የሚወሰዱትን ለዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔሮችና ሕዝቦች አንድነት ምስረታ መንገድ የጠረጉ እንቀጾችና ንዑስ እንቀጾች በወጉ ለመገንዘብ የሚያስችል ዕድል ከገጠመው ህብረተሰብ መካከል፤ ዛሬ ዛሬ እንደሚታየው ለትንሽ ለትልቁ የመብት ጥያቄ አገር አውዳሚ ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ የሚጣደፉ ወገኖችን አናገኝም ነበርና ነው፡፡

ስለዚህም፤ ሥርዓቱን እንደስርዓት በጸረ የአገር እንድነት ፈርጀው ሊያስወግዱት እንደሚፈለጉ የሚናገሩት ተቃዋሚ የትምክህት ኃይሎችም ሆኑ መገንጠልን እንደብቸኛ  አማራጭ ከመውሰድ የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አመለካከት የሚመነጨውን ጽንፈኛ አስተሳሰብ ጋር ወደ ከርሰ መቃብር መውረድን የመረጡ የሚመስሉት የተቃውሞው ጎራ ቡድኖች፤ በተለይም ወጣቱ ላይ ለማሳደር የሚሞክሩትን አሉታዊ ተጽእኖ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ፤ ሕገ መንግሥታዊ እሳቤን የማስረጽ ተጨባጭ ተግባራትን የመከወን ጉዳይ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ የቤት ስራችች መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ይህን ስል ደግሞ፤ ሕገ መንግሥቱ የኛን አገር አጠቃላይ ሁኔታ በቅጡ ከማገናዘብ በመነጨ የጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ የተረቀቀና ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት እንዲያመቻቸው ሲሉ በሚያናፍሱት ተራ አሉባልታቸው የህወሀት(ኢህአዴግ መሪዎች ጫካ ውስጥ  የነደፉት የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ…›› ለማስመሰል እንደሚሞክሩት እንዳይደለ በተለይም ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የሚረዳበትን ሕገ መንግሥታዊ አስተሳሰብ የማስረጽ ስራ በስፋት እና በጥልቀት መስራት እስካልተቻለ በሥርዓቱ ላይ ሲቃጣ የሚስተዋለውን ተደጋጋሚ አደጋ ጨርሶ የሚያስቀር ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አዳጋች ነው። ሕገ መንግሥቱ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በእርስ ተፈቃቅደው፤ ተከባብረውና ተፈቃቅረውም ጭምር ለመኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአገር አንድነት ለመፍጠር እንደማእዘን ድንጋይ የሚቆጠሩ እጅግ በጣም ጠቃሚ እሴቶችን መሰረት አድርጎ የተራቀቀ የቃል ኪዳን ሰነዶችን ስለመሆኑ፤ ገና ከመጽደቁ በፊት ጀም ያረጋገጡልን እንደነ አቶ ክፍሌ ዳጆ፤ፕፌሰር እንድሪስ እሸቴና ዶክት ፋል ናሆም ዓይነቶቹ ከተላያየ ብሔር ብሐረሰብ የወጡ ስመጥር ምሁራን እንደነበሩም ጭምር ወጣቶቻችንን የማሳወቅ ጉዳይ ቸል መባል የለበትም ማለቴ ነው፤

ከዚህም አኳያ እንደሀገር መስራት የሚጠበቅብንን ያህል ሳንሰራ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በቅርቡ የኢፌድሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን እንደ አዲስ ካዋቀሩበት የአደረጃጀት ለውጥ ጋር በተያያዘ መልኩ፤ ‹‹የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል..›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ተቋም እንደተመሰረተ ይፋ መደረጉን ግምት ውስጥ በማስገባ ወደፊት የሚጠበቅብንን የቤት ስራ በተሻለ መልኩ ለመከወን የማንችልበት ምክንያት እንደማይኖር ግን ይሰማኛል፡፡

ስለዚህ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር የተቋቋመው አዲሱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዘግይቶም ቢሆን እንዲመሰረት መደረጉ የሚደገፍና እሰየው የሚያሰኝ ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም፤ ተቋሙ እንዲመሰረት የተደረገበት ተግባርና ሃላፊነት ሕገመንግስታዊ እሳቤዎችን በማስረፅ ረገድ እስከዛሬ ድረስ ይስተዋል የነበረውን ሰፊ ክፍተት የማጥበብ አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ያመለክታልና ነው፡፡

በሌላ አነጋገር፤ ይህች አገር የምትመራበት ሕገ መንግሥት ስለደነገጋቸው የቡድንም ሆነ የግለሰብ መብቶች ማረጋገጥ ስለሚቻልበት አግባብ በቂ ግንዛቤ ሳንጨብጥ፤ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰማራት‹‹ ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም›› ተደርጎ ይቆጠራልና ተቋሙ ፈርጀ ብዙ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብና እንደ መልካም ባህል እየዳበረ መሄድ የግድ መሟላት ካለባቸው ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው፤ በተለይም ለሕገ መንግሥታዊ እሳቤ ልዕልና ዘብ የሚቆም ህብረተሰብን የማፍራት ጉዳይ እንደ ቁልፍ ተግባር ሊወሰድ ይገባል ሲሉ የፖለቲካዊ ሳይንስ ሊሂቃን ይመክራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ኢህአዴግ እራሱ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ባካሄደው የ1993ቱ ተሃድሶ ውይይት‹‹የዲሞክራሲያዊ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ባቀረበው የንድፈ ሀሳብ መጽሀፉ ላይ የሕግ ወይም ደግሞ የሕገ መንግሥታዊ እሳቤ ልእልና በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲረጋገጥ ማድረግ ሳይቻል ስለ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ  መብቶች መከበር አለመከበር ጉዳይ መነጋገር ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ከመሆን ያለፈ ትርጉም እንደማይኖረው የተተነተነበት አግባብ እንደነበር ማታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እናም፤ ዲሞክራሲያዊ የቡድን እና የግለሰብ መብቶችን የማረጋገጥ-አለማረጋጥ ጥያቄ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ የመሆኑን ያህል፤ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደወሳኝ የማእዘን ድንጋይ የሚቆጠረውን ሕገ መንግሥታዊ አስተሳሰብ የማስረጽ ተግባርም በቅድሚያ መሰራት ያለበት አንገብጋቢ ሥራ ነው የሚለው ነጥብ ላይ ልናሰምበት ይገባል፡፡ ስለዚህ አሁን የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄም፤ ይልቁንም ደግሞ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና እንዲሁም የአጋር ፓርቲዎች በአመራር ሰጭነት ቦታ የሚያስቀምጧቸው የሥራ ኃላፊዎች ሁሉ፤ ለሕገ መንግሥታዊ አስተሳሰብ ተገቢ ክብር በመስጠት ረገድ ለሌላው ዜጋ ወይም ህብረተሰብ አርአያ ሆነው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ቢቻል ምናልባትም ከዚህ ቀደም የነበሩ ድክመቶችን የሚያጠብ አወንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

እንግዲያውስ ኢህአዴግ እና መንግሥት የጀመሩትን በጥልቀት የመታደስ መርሃ ግብር ለማሳካት ሲባል ሕገ መንግሥታችንን መላው ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘለቄታዊ የጋራ እጣ ፈንታቸው መቃናት ሲሉ አንድ ጠንካራ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው ስለሚያሰኙት፤ እጅግ በጣም ጠቃሚ ፌደራላዊ እሳቤዎቹ ትርጉም ያለው የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣ ውይይትና አስተምህሮት መካሄድ አለበት። እናም መጭው ጊዜ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለእያንዳንዱ የአገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩል መጠን የሚያስፈልጋቸው የጋራ ህልውናቸው ዋስትና እንጂ፤ ያኛውን ወይም ደግሞ ይኼኛውን ወገን ይበልጥ ለመጥቀም፤ አሊያም ለመጉዳት የሚያስችል ይዘት የተካተተበት እንዳልሆነ ይልቁንም ወጣቱ የህብረተሰባችን ክፍል በተሟላ መልኩ እንዲገነዘብ ለማድረግ የሚያስችል ህገ መንግስታዊ እሳቤዎችን የማስረጽ ስራ መሰራት አለበት። መዓ ሰላማት!