ግብጽ ፈጣን የህዝብ ቁጥርን ለመግታት የቤተሰብ ምጣኔ ላይ ትኩረት ሠጥታ እየሠራች ነው

ግብፅ ፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገትን ለመቆጣጠር የቤተሰብ ምጣኔ  መርሃ ግብር   ላይ በትኩረት እየሰራች እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የግብጽ የህዝብ ቁጥር አሁን ላይ ከ93 ሚሊየን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህ አሃዝ  እኤአ በ2030 128 ሚሊየን ሊደርስ እንደሚችል የግብፅ ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

የ42 ዓመቷ ወይዘሮ ማሃሲን አብዶ በግብፅ ሰሜን ምዕራብ ገጠራማ አካባቢዎች ከሚኖሩ እናቶች አንዷ ናቸው፡፡ 10 ልጆችንም በሰላም ተገላግለዋል፡፡

የግብጽ  መንግሥት በዋናነት ለእናቶች  ስለቤተሰብ ምጣኔ እና የወሊድ ቁጥጥር የግንዛቤ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን   የአገሪቱን  የወሊድ  መጠን ለመግታት  ጥረት እያደረገ ነው  ፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የወሊድ ምጣኔው በከፍተኛ ሁኔታ  መጨመሩን ተከትሎ የፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ አስተዳደር ለቤተሰብ ምጣኔ ስራዎች ትኩረቱን እንዲያደርግ እያስገደደው ይገኛል፡፡

አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገሪቱ ገጠራማ ክፍሎች ላይ የወሊድ ምጣኔው እጅግ ከፍተኛ ሲሆን እናቶች በአማካይ ከ10 እስከ 12 ልጆችን እንደሚወልዱ ነው የሀገሪቱ ብሄራዊ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት  የሚያመለክተው፡፡

ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ጥግግት ከሚስተዋልባቸው የአረብ ሃገራት መካከል ግብፅ አንዷ ናት፡፡

ባለፈው ወር ኤጀንሲው ባቀረበው ሪፖርት  ግብፅ  ባሏት ህዝቦች ላይ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን አዲስ የተወለዱ ህጻናትን ተቀብላለች፡፡

ይሁንና ይህ የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር በተመጣጠነ ሁኔታ ማደግ ይጠበቅበታል፡፡

ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ባለፈው ወር ከሀገሪቱ ወጣቶች ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት ሀገሪቱን ክፉኛ እየተፈታተኗት ከሚገኙ ነገሮች መካከል ሽብርተኝነትና የህዝብ ቁጥር እድገት በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ አንስተዋል፡፡

የግብፅ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የሀገሪቱን የወሊድ ምጣኔ ወደ 2 ነጥብ 4 በማድረስ መንግስት እኤአ እስከ 2030 ድረስ ከ200 ቢሊየን የግብጽ ፓውንድ ማለትም ከ11 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተጨማሪ ወጪን ለማዳን  ግብ መጣሉን ይገልጻል፡፡

ሚኒስቴሩ አሁን የሚስተዋለውን አስደንጋጭ የወሊድ ምጣኔ አሃዝ ዝቅ እንዲል ለማስቻል በቤተሰብ ምጣኔ ዙሪያ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ከ6 ሺህ በላይ ክሊኒኮችን ስራ ያስጀመረ ሲሆን እናቶች ነፃ ምርመራና የምክር አገልግሎትን እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡

እናቶች ከዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ጋር ያላቸው ቁርኝትን ለማሳደግም በየሆስፒታሉና ጤና ጣቢያዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ታሪክ አቡሌላ የተሰኙ አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ ተናግረዋል፡፡

የእነዚህ ሁሉ ድምር ስራዎች ውጤትም ሀገሪቱ እንዳሰበችው የምጣኔ ሃብት እድገቷ ከህዝብ ቁጥር እድገቱ ልቆ እንዲወጣ ያስቸለዋል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡( ምንጭ:ወርልድ ቪው )