ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የሊቢያ ወታደሮች በግብፅ ተያዙ

ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው የሊቢያ ወታደሮች በግብጽ መያዛቸው ተገለጸ ።   

ተጠርጣሪዎቹ በቅርቡ በተገደሉ ግብጻውያን ፖሊሶች ላይ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ስትል ግብፅ ከሳለች፡፡

ጎረቤት ሃገር ግብፅ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች የበርካታ ዜጎቿን ሕይወት አጥታለች፡፡ በሃገሪቱ የእምነት ቦታዎችና የጥበቃ አካባቢዎች በተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶች  የሃይማኖት መሪዎች፣ ምዕመናን እና የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የበርካታ ዜጎቿ ህይወት ማለፉን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው ባለፈው የፈረንጆቹ ጥቅምት 21 ላይ የሃገሪቱ መንግስት 16 የፖሊስ ኃይሎቹ በአሸባሪዎች ጥቃት ተገድለውብኛል ያለ ሲሆን ሶስት የሃገሪቱ የደህንነት ሰዎች ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር 16 ሳይሆን ከ52 በላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የግብፅ መንግስት ባለፈው ወር ላይ በተፈፀመው የሽብር ጥቃት ላይ እጁ አለበት ያለውን የሊቢያ ወታደር በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

እጁ አለበት የተባለው ሊቢያዊ ወታደር አብደልራሂም ሞሃመድ አል መስማሪ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን የመጣበት አካባቢም ከምስራቅ ሊቢያ ደርና ከተማ እንደሆነ እና እዛም ሲሰለጥን እንደቆየ የግብፅ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡

ተጠርጣሪውን ሲያሰለጥን የነበረው አንሳር አል ኢስላም የተባለው ቡድን በባለፈው ወር ጥቃት ላይ ኃላፊነቱን እንደወሰደ የዘገበው ሮይተርስ ወጣቱ ተጠርጣሪ ወታደር አል ሃያት ከተባለ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ቡድኑ የአልቃኢዳን ርዕዮተ ዓለም የሚከተል እንደሆነና ቀንደኛ ጠላታቸውም አሜሪካ እንደሆነች ተናግሯል፡፡

ቡድኑ የጽንፈኛው አይ ኤስ ታቃዋሚ እንደሆነም ተናግሯል፡፡‹‹ሃይማኖቴን መሠረት አድርጌ ከተዋጋሁ እንደምሸለም ተስፋ አደርጋለሁ›› ያለው መስማሪ ቡድኑን እኤአ በ2014 እንደተቀላቀለም ተናግሯል፡፡ 

የሃገሪቱ መንግስትም ባለፈው ጥቅምት ወር በተፈፀመው የሽብር ጥቃት አጻፋ ላይ 15 ታጣቂዎችን እንደገደለና 29 ታጣቂዎቹን እንደማረከ በመግለፅ ሁሉም በደርና ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው ብሏል፡፡( ምንጭ: ሮይተርስ)