‹‹እኔ ጨረቃውን ሳሳያችሁ፤ ጣቴን አትመልከቱ››

ክፍል አንድ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈሚ ኮሚቴ፤ ታህሳስ 21፣ 2010 ዓ.ም ያወጣው ድርጅታዊ መግለጫ፤ የድርጅቱን መሠረታዊ ችግሮች እና ችግሩን ለመቅረፍ መወሰድ ያለበትን እርምጃ የሚያመለክትም ነው፡፡ በመግለጫው የሰፈረውን የውሳኔ ሐሳብ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉት ያለውን ሥራ ጋር በማገናዘብ፤ ዶ/ር አቢይ የድርጅታቸውን መስመር እና ውሳኔ ተከትለው የሚሄዱ እና በአጭር ጊዜም ስኬት ያስመዘገቡ መሪ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 21፣ 2010 ዓ.ም ለ18 ቀናት ስብሰባ ተቀምጦ፤ ሐገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ሰፊ እና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ በሐገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤ እና መፍትሔዎቻቸው ላይ መክሮ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሐገራችን የሚታየውን ለውጥ በተጀመረው ስፋት እና ግለት ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተኑ ችግሮች እየታዩ መምጣታቸውን ይገነዘባል›› ካለ በኋላ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፤ ሐገሪቱ እጅግ በሚያስጎመዥ እና አሳሳቢ በሆኑ ወቅታዊ ችግሮች ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሶ፤ ‹‹ይሁንና ይህ የሚያስጎመዥ የዕድገት እውነታ… ለሁሉም ማህበረሰቦቻችን የስጋት ምንጭ መሆን በጀመረ አዲስ ክስተት መልክ የሚገለፅበት አዝማሚያ ሰፋ ብሎ ታይቷል›› ይላል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደ መጣ ባደረገው ግምገማ ያረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህ ችግር በዋነኛነት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይ እና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተከተሰተ እንደሆነ እና ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንዲሆን የማድረጉን ጥረት ለአደጋ ያጋለጠ ችግር ሆኖ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በላይ ጊዜ ባካሄደው ግምገማ በመላው የአገራችን ህዝቦች ከባድ ተጋድሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅ እና ለማስፋት፤ እንዲሁም በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎች እና ስጋቶች ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ መግባባት ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

‹‹የሐገሪቱ ስርዓት ለበላይነት እና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል›› ያለው ይኸው መግለጫ፤ የባላይነት ሆነ የበታችነት ስሜት የማይፈጠርበት ስርዓት መገንባቱን እና ይህንን መሰረታዊ መርሆ የሚነካ ማንኛውም ዝንባሌ፤ ከመኖቆር ውጭ ሌላ ውጤት የማያስገኝ በመሆኑ፤ በማንኛውም ሽፋን ይህንን የእኩልነት ስርዓት ለማዳከም የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት እንደ ሌለውና ሊመከት እንደሚገባው ወስኗል፡፡ በብሔር ህዝብ እና ድርጅት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን እንቅስቀሴ ማክሰም እንደሚገባም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ያሉ ጥገኞችን ያለ ልዩነት እና ማመንታት መታገል እንደሚያስፈልግ አትቶ ነበር፡፡

ከዚያም አልፎ ዴሞክራሲውን ማስፋት እና ማጠናከር ሲገባ፤ በተለያዩ መንገዶች የማጥበብ አዝማሚያም መስተዋሉን የጠቀሰው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ፤ ልዩ ልዩ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች ወይም ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ፣ ህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ ዕድል ከፍቶ እያለ አመራሩ ዴሞክራሲውን የማስፋት ግዴታውን ባለመወጣቱ፤ ችግሮች ወይም ልዩነቶች በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ፤ ለሰላማችን መታወክ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል ይላል – መግለጫው፡፡

አያይዞም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች በልዩ ልዩ ሰበቦች የሰላም መደፍረስ እየተፈጠረ፤ ችግሩ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ያለው መግለጫው፤ ይህም በህዝቡ ዘንድ የስጋት መንፈስ እና ጭንቀትን ፈጥሯል ብሏል፡፡

ከበየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሞት፣ ከንብረት ውድመት በተዘለለ ሐገራዊ ሕልውናችንን ለአደጋ ያጋለጠ ችግር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ህገ መንግስታዊ ስርዓታችንን በማጠናከር፤ እየተዳከመ የመጣውን የአስተሳሰብ ብዝሃነት በአግባቡ እንዲገለፅ እና ለዚህ የሚረዳ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ጥረት መደረግ እንዳለበት አትቶ ነበር፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል የሃገራችን ሚዲያ እና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የገመገመው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ በዚህ ረገድ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወሰድ ወስኗል፡፡

አመራሩ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በመገንባትና በህገ መንግስታዊ ስርዓታችን ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እየተገባው የህዝብ የተደራጀ ሲቪል እንቅስቃሴ እንዳልተጠናከረ አረጋግጧል፡፡ በአገራችን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ ዋስትና የሚኖረው ከአዋጅ አልፎ ህዝብ በተደራጀና ንቁ አኳኋን ሲሳተፍና ሲጠቀምበት በመሆኑ፤ የሲቪል ማህበረሰቡን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ሥራ መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሰረት በአገራችን የሚገነባው ዴሞከራሲያዊ ስርአት የሚታይበትን የሲቪል ማህበረብ ተሳትፎና ሁለገብ እንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉበት ችግሮች በማላቀቅ ማጠናከር እንደሚባ ታምኖበታል፡፡ አመራሩ የዴሞክራቲክ ተቋማት ግንባታና የህዝብ የተደራጀ ተሳትፎ የሞት የሽረት ጉዳይ እንደሆነ ተገንዘቦ ባለመንቀሳቀሱ የተፈጠረውን መሰረታዊ ጉድለት ለመፍታት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በሃገራችን በየደረጃው መካሄድ የሚገባቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ሃገራዊ ራዕይ በሚያስይዝ እና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በሚያጠናክር መልክ ባለመፈጸማቸው በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነት በማጠናከር ረገድ የተደራጀ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ሥራ አስፈፃሚው ወስኗል፡፡ ብሄረሰባዊ እና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየው ጉድለት በአፋጣኝ እና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንዳለበት ታምኖበታል፡፡ የዶ/ር አቢይ የመደመር መፈክር ትርጉሙ ይህ ነው፡፡

በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛ ምስጢር የሕዝብን ተሣትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ያለው መግለጫው፤ በዚህም መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የህዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘት እና ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተከታታይ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን፤ ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርም ወስኗል፡፡

እናም ዶ/ር አቢይ አህመድ እነዚህን ውሳኔዎች፤ ከልብ ተቀብለው ፈራ ተባ ሳይሉ ለማስፈጸም የተነሱ መሪ ናቸው፡፡ እንዲሁም ለውጡ የሚጠይቀውን እርምጃ ለመውሰድ የማያመነቱ፤ ጠንካራ የህዝብ እና የሐገር ፍቅር ያላቸው፤ ለህዝቡ ቅርብ ለመሆን ዕድል የሚከፍት ‹‹ሲምፒሊሲቲ›› የተላበሱም ናቸው፡፡ የየአካባቢውን ህዝብ ባህል እና ታሪክ የሚያውቁ (ለማወቅ የሚጥሩ ሰው መሆናቸው)፤ ቋንቋውን ተጠቅመው የሚያነጋግሩ መሪ በመሆናቸው ወዘተ በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡

ዶ/ር አቢይ የድርጅታቸውን ውሳኔዎች ሲያስፈጽሙ፤ ዶ/ር አቢይ መሆናቸውን ሽረው፤ መልክ የለሽ ሆነው አይደለም፡፡ ከቀዳሚዎቹ የድርጅቱ አመራር ጋር ለመመሳሰል ወይም ለመለየት ሳይሆን ራሳቸውን መስለው ለመሥራት የሚሞክሩ ሰው በመሆናቸው የተለየ አመራር የሚከተሉ አስመስሏቸው ይሆናል እንጂ ከድርጅታቸው የወጡ አይደሉም፡፡

ለሦስት ዓመታት በአመጽ ሲናጥ ከከረመው የሐገራችንን ክልል (ኦሮሚያ) የመጡ  መሪ በመሆናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪም እስከ አጥንት ዘልቆ የሚገባ የህዝብ ምሬት እና ብሶቶትን እየሰሙ የቆዩ ሰው በመሆናቸው፤ ህዝብን በሽንገላ አረጋግቶ መመለስ እንደማይቻል ተረድተው ለውጥ ለማምጣት ቆርጠው የተነሱ መሪም ናቸው፡፡ በድርጅታቸው የተሐድሶ ግምገማ የተለዩትን ችግሮች ከመረዳት ባሻገር፤ ለየት ባለ ዘዬ ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሚሞክሩ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚሞክሩ ሰው ናቸው፡፡ የድርጅታቸው ህልውና ሊረጋገጥ የሚችለው፤ የህዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ እንጂ በመሸንገል አለመሆኑን ከልብ አምነው የተቀበሉ የህዝብ ልጅ የሆኑ መሪ ናቸው፡፡

የድርጅታቸውን ውሳኔ፤ በራሳቸው የአጽንዖት እና የገላጻ ጥበብ እየቃኙ ለመሥራት የሚሞክሩ ናቸው፡፡ አሁን የሚታየው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እና ሐገራዊ መግባባት የተገኘው በዚህ መልክ በመስራታቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ምዳሩን ማስፋት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር መሥራት፣ እስረኛ መፍታት፤ የዴሞክራሲ ስርዓቱን ማጠናከር (ተቋማትን ማጠናከር፣ የተቋማትን ለገልተኛነት እና የህዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ) ህገ መንግስቱን ማክበር እና ማስከበር (ልጽነት እና ተጠያቂነት)፣ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር፤ ጠባብ ብሔርተኝነትን እና ትምክህትን መታገል፤ የኢኮኖሚ ልማቱን ማጠናከር እና የተቀመጡትን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ማሳካት ወዘተ የድርጅታቸው ውሳኔዎች ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በድርጅታቸው የተሰጣቸውን እነዚህ ኃላፊነቶች ባለፉት ሦስት ወራት ሥራዎቻቸው ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ትልቅ ስኬትም አስመዝግበዋል፡፡ ዶ/ር አቢይ አህመድ የፖለቲካ ማበረሰባችን ትልቁ ዓላማ የሆነውን፤ ለሌሎች የልማት ሥራዎች መሠረት የሚሆነውን ሐገራዊ ህልውናን ከማስጠበቅ ጀምሮ፤ የልማት ግቦቻችንን ለማሳካት እንቅፋት ሆኖ የታያቸው፤ ጥላቻ እና ቂም ነው፡፡ ጥላቻ እና ቂምን ለማስወድ ፍቅርን መስበክ አስፈላጊ ነው፡፡ የስስት እና የእጦት መንፈስ እየተጠናከረ፤ በእኔ ክልል ሌላ ሰው ማየት አልፈልም የሚል አስተሳሰሰብን ማስወድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ትልቁን ስዕል ማሳየት እና መደመርን መስበክ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን እክል ሳያስወግዱ ወደፊት መራመድ አይቻልም፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያ ትኩረታቸው ያደረጉት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡

ዶ/ር አቢይ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው የሰጡት ማብራራያ ይህን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እርሳቸውን ለመደገፍ በመስቀል አደባባይ ለገተኘው ህዝብም ያቀረቡት ጥሪ ‹‹ከእኔ ክልል ውጣ›› የሚል ሐሳብ እንዲወገድ ነው፡፡ የአስተዳደር ወሰንን ድንበር አድርጎ በመውሰድ የሚፈጠሩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ከዚህ አስተሳሰብ እንውጣ›› ብለዋል፡፡ ይህ ኢህአዴግ በተሐድሶ ችግር አድርጎ ከለያቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነበር፡፡ ኢህአዴግ፤ ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በመረጡት ክልል ተዘዋውረው ለመሥራት እና ለመኖር የሚችሉበት ዕድል አለመኖሩን ጠቅሶ፤ ችግሩ በአፋጣኝ እንዲስተካከል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ህገ መንግስትን የማክበር እና የማስከበር ሥራ ሊጀመር የሚችለውም ይህን ኋላ ቀር አመለካከት ከማስወገድ እርምጃ ነው፡፡ ዶ/ር አቢይ የተለመዱ ወይም የተሰለቹ፤ ‹‹ጠባብነት ወይም ትምክህት›› የሚሉ የጨረቱ ቃላትን ባያነሱም፤ የሚታገሉት ግን ኢህአዴግ ዋነኛ ችግር አድርጎ ‹‹የጠባብነት ወይም የትምክህት›› ችግሮችን ለማስወገድ ነው፡፡

ዶ/ር አቢይ በቅርቡ ከደቡብ ክልል ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ አድሎ ሲኖር የማህበረሰቡ ህይወት የተባላሸ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በርግጥ፤ አንድ የመንደር አለቃ፣ የቀበሌ ሹም ሆነ የሐገር አስተዳዳሪ ሥልጣኑ በህዝብ ፈቃድ ያልተባረከ ሲሆን ወይም የሁሉንም አባላቱን የጋራ ጥቅም በእኩልነት ለማስከበር በሚያስችል መርህ ተወስኖ ለማስተዳደር ካልቻለ፤ ችግር ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም፤ የብዙሃኑን ፍላጎት በማክበር፤ የመላውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር ዓላማ ይዞ ያልተነሳ መንግስት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፡፡ የአንድን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት አፍራሽ ነው፡፡ ግን እንዲህ ዓይነት ጥረት የሚደረገው የህዝብን  ሳይሆን የቡድኖችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚኖር ፍላጎት ነው፡፡

አንድን ህዝብ ከሌላው ለይቶ ለመጥቀም የሚሞክር መንግስት፤ በተጨባጭ በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ከመጥቀም አልፎ፤ እወክለዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ ሁለት ህዝቦችን እኩል ለማየት የማይችል አንድ የፖለተካ ኃይል ወይም የክልል መንግስት፤ በራሱ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ዞኖችን፣ ወረዳዎችን፤ ክፍለ ከተሞችን፣ መንደሮችን፣ ቡድኖችን፣ ቤተሰቦችን እና ግለሰቦችን እኩል ለማየት አይችልም፡፡ ይህ መንግስት በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ላይ የቆመ ባለመሆኑ፤ እወክለዋለሁ ወይም እጠቅመዋለሁ እያለ ስሙን የሚጠራውን ህዝብ መነገጃ ያደርገው ይሆናል እንጂ የማህበረሰቡ አባላትን ጥቅም ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ዛሬ ባይሆን ነገ፤ እዚህ ባይሆን እዚያ፤ ውሎ አድሮ እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ ተጻራሪ ኃይል መሆኑ አይቀርም፡፡

በሌላ በኩል፤ ሁሉንም ማህበረሰብ በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ለመምራት የሚጣጣር መንግስት ከሆነ፤ ይህ መንግስት በቋንቋም ሆነ በባህል ለማይመስሉት፤ በአጭሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊጠቅም የሚችል መንግስት ይሆናል፡፡ በመሆኑም፤ የራሱን ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚችል መንግስት፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ የሚመራ መንግስት ነው፡፡ ዣን ፖል ሳርትር፤ ‹‹አንድ ሰው ለራሱ ሲመርጥ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ይመርጣል›› ያለው ለዚህ ነው፡፡

የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት የማይከተልና በዴሞክራሲያዊ መርሆች የማይመራ መንግስት፤ ውሎ አድሮ በስሙ በሚነግድበት ህዝብ መካከል በሚኖሩ ልዩነቶች እየተሳበ ሚዛን የሚስት እና ከአንዱ ወይም ከሌላኛው ንዑስ ቡድን ጋር በመወገን፤ በመደብ፣ በቋንቋ፣ በብሔር ወይም በሌሎች ልዩነቶች ተጠልፎ የአንድ ቡድን አገልጋይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ራሱን ከዚህ አይነት መሰናክል ለማዳን የሚያስችል የስነ ልቦና ወይም የመርህ ገደብ ሊኖረው ስለማይችል ሁሌም ሲሳሳት ይገኛል፡፡

ስለዚህ አንድ መንግስት እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ጭምር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያገለግል የሚችለው፤ ሁሉንም በእኩልነት ለማገልገል የሚያስችል ወይም የሰው ልጆችን በመላ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መርህ የሚከተል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ እይታ አንድን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት፤ ሁሉንም የሰው ልጆች ሁሉ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት ነው፡፡ አንድን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል መንግስት፤ በመርህ የሚመራ እንጂ በአድሎ የሚሰራ መንግስት አይደለም፡፡ ለአንድ ቡድን ጠቃሚ ሆኖ የተገኘ ቡድን፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መንግስት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ የሚመራ መንግስት የአንድ የተወሰነ ህዝብ አገልጋይ ለመሆን አይችልም፡፡ ዶ/ር አቢይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳው የሚፈልጉት እውነት ይህ ነው፡፡