ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – በ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የሚተገበረው 4ኛው ዙር የንፁህ መጠጥ ውሀ እና ሳኒቴሽን (ኮዋሽ) ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡
ፕሮግራሙ 18 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ ከፊንላንድ መንግስት በተገኘ ድጋፍ እና 22 ነጥብ 6 ሚሊየን ዩሮ ደግሞ በክልል መንግስታት የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም በአጠቃላይ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።
4ኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ከሚተገበርባቸው አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረስቦችና ህዝቦች ክልል በተጨማሪ ሲዳማ ክልልን በማካተት እንደሚተገበር ተነግሯል።
በፕሮጀክቱ ለ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውሀን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል።
ካለፉት 3 ዙሮች ለየት ባለ መልኩ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልገው በጀት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እንዲያልፍ ከስምምነት መደረሱንም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ከንፁህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን በተጨማሪ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኦውቲ ሆሎፔኒን በበኩላቸው፣ የፊንላንድ መንግስት በክልሎች ለሚተገበረው የኮዋሽ ፕሮግራም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
(በትዕግስት ዘላለም)