5ኛው ከተማ ዐቀፍ የንባብ ሳምንት በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ሊካሄድ ነው

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) አምስተኛው ከተማ ዐቀፍ የንባብ ሳምንት ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የሚካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የንባብ ሳምንቱ ከግንቦት 24 እስከ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የሚካሄድ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስፋው ለገሰ ገልጸዋል።

የመርኃ ግብሩ ዋነኛ አላማ ማኅበረሰቡ የንባብ ባህሉን እንዲያዳብርና በከተማው የሚገኙ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት እና መጻሕፍት ሻጮች ጠንካራ ትስስር እንዲኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአምስተኛው ከተማ ዐቀፍ የንባብ ባህል ሳምንት 48 ተቋማት የመጻሕፍት አውደ-ራዕይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

በአውደ-ራዕዩ 25 የመንግሥት ቤተ-መጻሕፍት እና 23 የግል መጽሐፍ ሻጮች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ኃላፊ ውብአየሁ ማሞ የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለመፍጠር እና የተሻለች ሀገር ለመገንባት የማንበብ ባህልን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ለአብርሆት ቤተ መጽሓፍት “ሚሊዮን መጽሐፍ ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ከ500 ሺሕ በላይ መጻሕፍት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

አምስተኛው የንባብ ባህል ሳምንት “በማንበብ የዳበረ አእምሮ ለኅብረ ብሔራዊ መግባባት” በሚል መሪ ኃሳብ እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።