60 ባለ ልዩ ተሰጥዖ ወጣቶች ታኅሣሥ 22 ይመረቃሉ

ታኅሣሥ 11/2015 (ዋልታ) በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሲደገፉ የነበሩ 60 ባለ ልዩ ተሰጥዖ ወጣቶች ታኅሣሥ 22 እንደሚመረቁ ተገለጸ።

ለወጣቶቹ ለሦስት ሳምንታት በተግባር ተደግፎ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ክህሎታቸውን ያሳደገ መሆኑም ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር ወጣቶቹ ተመርቀው ሲወጡ ያላቸውን ተሰጥዖ ወደ ቢዝነስ የሚቀይሩበትን ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሥራ ወቅት የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት የፊታችን ሐሙስ በሳይንስ ሙዚየም ዘለላ በተሰኘው የአድቮኬሲ እና የትስስር ፕሮግራም ላይ ስራቸውን እንደሚያስተዋውቁ እና ትስስር እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው ተቋሙ የያዘውን የቴክኖሎጂ በላይነትን እቅድ ለማሳካት ታዳጊዎች ላይ መስራት እንደሚገባ ገልጸው ታዳጊዎች መፍጠር እንዲችሉና የፈጠራ ውጤታቸውን ወደ ገበያ ማውጣት እንዲችሉ ባቋቋምነው የሳይበር ታለንት ማዕከል በኩል በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

4ኛው ዘለላ ወርሃዊ የፖሊሲ አድቮኬሲ እና የትስስር ፕሮግራም የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚዘጋጅ መሆኑም ታውቋል።

ከታኅሣሥ 13 እስከ 21 የተመራቂ ተማሪዎች የፈጠራ ውጤቶች በሳይንስ ሙዚየም እንደሚቀርቡ የተነገረ ሲሆን ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናልም ተብሏል።

በትዕግስት ዘላለም