8ኛው ዙር የሀገሪቱ የጤና ወጪ ጥናት ማስጀመሪያ ይፋ ሆነ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – የጤና ሚኒስቴር 8ኛው ዙር የሀገሪቱን የጤና ወጪ ጥናት ማስጀመሪያ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ላይ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከመንግስት እና ከግል ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የጤና ወጪ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና ለጤናው ዘርፍ የሚውለውን የሀብት ፍሰት ለመከታተል በርካታ ሃገራት የሚጠቀሙበት ዘዴ ሲሆን፣ ዘዴው ለዘርፉ የሚወጣውን አጠቃላይ ሀብት ከመነሻው ማለትም ሀብቱን ከሰጠው አካል እስከመጨረሻው ማለትም ሀብቱ ለምን ጥቅም እንደዋለ በዝርዝር ይመረምራል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም የወጣው ወጪ በማን ወይም በየትኛው አካል እንደሚተዳደርና ለተጠቃሚው የሚቀርቡ የጤና አገልግሎቶችም በየትኛዎቹ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደተሰጡ በዝርዝር ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ተደራሽነትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመላው ህብረተሰብ ለማዳረስ በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት፣ የጤና ወጪ የጥናት ግኝቶችን በየጊዜው ለሚወስዳቸው የፖሊሲ ውሳኔዎችና የሀብት አመዳደብ ሥርዓት በግብዓትነት ሲጠቀምባቸው መቆየቱና አሁንም በመጠቀም ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደው የአሁኑ ዙር የጥናት ወጪ የሚሸፈነው በመንግስት እና በዘርፉ የልማት አጋሮች ይሆናል፡፡