ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል እንዲችል ሊሠራ ይገባል – ጤና ሚኒስቴር

 

 

የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በጋራ ያካሄዱት የ6 ወር የስራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

ባለፉት 6 ወራት ለጤና ሚኒስቴር ተጠሪ በሆኑ ተቋማት የተከናወኑ አበይት ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና የታዩ ክፍተቶች ተገምግመዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር በጋራ የተደረገው ርብርብ አበረታች መሆኑ ተገምግሟል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አሁን ላይ የታዩ መዘናጋቶችን ለማስቀረትና ህብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ መከላከል እንዲችል ሊሠራ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

የህክምና መሳሪያዎች ግዥና ተከላን አስመልክቶ ክፍተቶች የሚታዩበት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ከመድኃኒት ጋር በተያያዘም አሠራሩን ለማዘመንና አቅርቦቱን ለማሻሻል ባለፉት 6 ወራት አበረታች ጥረቶች ቢታዩም የጤና ተቋሟትን ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ ያሟላ ባለመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።

የጤና መድህን አገልግሎትን በተመለከተ በክልሎች ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተጀመረው ንቅናቄ አበረታች ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተነስቷል፤ አዋጁን የማጸደቅ ሥራ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው በግምገማው ተገልጿል፡፡

ከኤች አይ ቪ/ ኤድስ ልየታ እና ምርመራ ጋር በተያያዘም በቀጣይ የእቅድ ዘመን ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ እንዲሁም የድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅንጅታዊ ምላሽ አሰጣጥ በቀጣይ የተቋማቱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንደሚገባው በግምገማው ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት 6 ወራት በምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተከናወኑ ተግባራትና የተወሰዱ እርምጃዎች ተገምግመዋል፤ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በዋናነት ማሳደግ እንደሚገባ ተነስቷል።

በታቀደው መሰረት ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች የተሰበሰበው ደም እየጨመረ መምጣቱ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት የበለጠ መስራት ይገባል ተብሏል።