ሚኒስትሩ በ12ኛ ክፍል ውጤት ዙሪያ ከጋምቤላ ክልል ካቢኔ ጋር ተወያዩ


ጥቅምት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የትምህርት ሚኒስትር ኘሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከጋምቤላ ክልል ካቢኔ ጋር በ12ኛ ክፍል ውጤትና በትምህርት ዘርፉ ላይ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በመድረኩ ክልሎች ከዚህ ቀደም በ12ኛ ክፍል ፈተና የሚያስመዘግቡት ከፍተኛ ውጤት በአሁኑ ወቅት እጅግ መቀነሱን ጠቅሰው ይህም የሆነበት ምክንያት ፈተናውን ከስርቆትና ከማጭበርበር ለማፅዳት በተደረገው ዘመቻ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም ትምህርትን ከስርቆትና ከማጭበርበር የማፅዳቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ካቢኔ አባላትም በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደ ክልል የትምህርት ሴክተሩ ላይ ያሉ ችግሮችን አንስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የመምህራን ብቃት ማነስ፣ የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ የተማሪዎች ስነምግባር ብልሹነት ፣የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት አለመሻሻል በውይይቱ ከተጠቀሱት ችግሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞጆ ኡጁሉ በበኩላቸው የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት በየእርከኑ ያሉ ሴክተሩን የሚመሩ አካላት የተጣለባቸውን የመሪነት ግዴታ በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ትምህርት ቤቶች መካከል መንግስት ካስገነባቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች እንደሆኑ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ተጨማሪ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት እየተገነባ መሆኑን መጠቆማቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይም ሚኒስትሩ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከመምህራን እንዲሁም በየትምህርት ቤት ካሉ የወላጅ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።